በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል - ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል - ትምህርት ሚኒስቴር
አርባ ምንጭ ፤ ነሐሴ 19/2015 (ኢዜአ):- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ውጤቶች መመዝግባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2015 በጀት ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ልማት ስራ አፈጻጸም በአርባ ምንጭ ከተማ እየገመገመ ነው።
በግምገማው ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የአጋር ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የትምህርት ዘርፉ ቁልፍ ስብራት የሆነውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት፣ዝቅተኛውን የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታን ወደ አራት ዓመት ከፍ ማድረግ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በትኩረትና በተልዕኮ መለየትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መውጫ ፈተናዎችን ማዘጋጀት ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ ማስቻል ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን በማንሳት።
በዚህም የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አዋጅ መጽደቁንና ይህን ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ እንዲሆን የሚያስችል ደንብ መውጣቱን ነው ዶክተር ሳሙኤል ያስታወሱት።
ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ ብቁ የሰው ኃይል በመመደብና ዩኒቨርሲቲዎችን በቴክኖሎጂ ከመደገፍ ባለፈ ተማሪዎች ለፈተናው እንዲዘጋጁ ከማድረግ አኳያም ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በዚሁም በ215 ፕሮግራሞች ፈተናውን ከወሰዱ 150 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ 60 ሺህ ወይም 40 በመቶዎቹ የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተቀረጹ ሪፎርሞችን ለመተግበር በተደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2016 የበጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆንን ጨምሮ በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።
ግምገማው እስከ ነገ ይቆያል።