ቀጥታ፡

በጦርነት እና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነን በክልሉ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮችን ያሳዩን የቀድሞ መሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2015 (ኢዜአ)፦ በጦርነት እና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነን በክልሉ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮችን ያሳዩን የቀድሞ መሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ  አቶ አረጋ ከበደን ርዕሰ መሥተዳድር አድርጎ ሹሟል። 

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወደ ሀላፊነት የመጡበት ወቅት ፈታኝ እና የጋራ ትብብርን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡ 

በጦርነት እና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሆነን በክልሉ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮችን ያሳዩን የቀድሞ መሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተለይም ለቀድሞው ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በሳል፣ የሰከነ እና ሆደ ሰፊ አመራር ሰጭነት ምክር ቤቱ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በሀላፊነት ዘመናቸው ክልሉ አሁን ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አውጥቶ የተሻለ እና የተረጋጋ ክልል ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በቅንነት እና በኅላፊነት እንደሚሠሩ አንስተዋል፡፡

የምጣኔ ሃብት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ችግሮች አሉብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የአማራ ክልል ከገጠመው ውስብስብ ችግር ለመውጣት የአባቶቻችንን ብስለት እና የሕዝባችንን ስክነት እንደመውጫ መፍትሔ እንጠቀማለን ነው ያሉት፡፡

አሁናዊ ችግሩ ክልሉን እና የሕዝቡን ሥነ-ልቦና የሚጎዳ በመሆኑ በፍጥነት ከችግሩ መውጣት ይገባል ብለዋል፡፡

የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ሕጋዊ የፌዴራል መንግሥትን ውሳኔ የሚጠብቅ እንጂ የሕዝብን ጥያቄ የሚዘነጋ እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ የክልሉን ሕዝብ ማህበራዊ እረፍት ለማምጣት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ የክልሉ ተወላጆች፣ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲረባረቡ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች፣ የክልሉ ሕዝብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ከክልሉ መንግሥት ጎን በመቆም ለሰላም እንዲሠሩ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

የብዙሃን መገናኛ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝቡ የሚገባውን እና የሚሻለውን ለማድረግ በጋራ እንሥራ ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ የፌዴራል መንግሥት እና ሌሎች ክልሎች የክልሉን ሕዝብ በማገዝ አብረው እንዲቆሙ ጠይቀዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም