በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል-አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል-አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 19/2015 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል አሁን የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግና እንዲፈቱለት እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።
ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር የመከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና መላ ህዝቡ በከፈለው መስዋዕትነት ሰላም መገኘቱን ተናግረዋል።
እንደ ትላንቱ ሁሉ የኢትዮጵያን ዕድገትና ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሌት ከቀን እየሰሩ ቢሆንም በህዝቡ አስተዋይነት ሰላም አግኝተን ወደ ተሟላ እንቅስቀሴ ገብተናል ብለዋል።
አሁን በክልሉ በተገኘው ሰላም ህዝብን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ በተከሰተው የሰላም መታጣት ውስጣዊ ችግራችን ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት አፈ-ጉባኤዋ ውጫዊ ግፊቱ ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ የነበረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
ባሳለፍናቸው መደበኛ ጉባኤዎች በተደጋጋሚ የተወያየንባቸው የህዝቡ ጥያቄዎች ተለይተው ያደሩ ቢሆንም ፈጥነን መፍታት ባለመቻላችንና ያልፈታንበትን ምክንያት በየጊዜው መረጃ ባለመስጠታችን ህዝባችንን አስቆጥቷል ብለዋል።
በመሆኑም ህዝቡ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ሁላችንም ልንረባረብና ልንሰራ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል።
ችግሮችን በሀይል ለመፍታት መሞከር ህዝቡን ለባሰ ጉስቁልና የሚያጋልጥ በመሆኑም ጥያቄ ያለው ሁሉ ችግሮችን በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመነጋገር እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላትም ችግሮችን ለይተን በመወያየትና መፍትሄዎችን በማስቀመጥ፣ እንዲሁም ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በቁርጠኝነት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለአንድ ቀን በሚካሂደው አስቸኳይ ጉባኤም በክልሉ ሰላምና ደህንነት ላይ እየተወያየ ሲሆን የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።