ቀጥታ፡

አትሌቶችቻችን በቡዳፔስት ያስመዘገቡት ድል አንድነት ለውጤት እንደሚያበቃ አስተምሮናል---የሐዲያ ዞን ወጣቶች

ሆሳዕና ፤ነሐሴ 19/2015 (ኢዜአ)፡- አትሌቶቻችን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገቡት ድል በአሸናፊነት ወኔ እና በጠንካራ አንድነት የተገነባ ሥነ ልቦና ለውጤት እንደሚያበቃ አስተምሮናል ሲሉ የሐዲያ ዞን ወጣቶች ተናገሩ። 

በቡዳፔስት ሐንጋሪ እየተካሄደ ባለው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገና በቡድን መስራት ከተቻለ በሌሎች መስኮችም ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐዲያ ዞን ወጣቶች ገልጸዋል።

በዞኑ ሆሳዕና ከተማ የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሄኖክ ሽፈራው በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሻምፒዮናው ባስገኙት ድል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ማየቱ አስደስቶታል።

አትሌቶቹ ተናበውና ተቀናጅተው በቡድን በሰሩት ሥራ ያስመዘገቡት ውጤት እንደሚያኮራም ገልጿል።

"የአትሌቶቹ ውጤት ኢትዮጵያውያን ሰላምና አንድነትን በማጠናከር በጋራ መስራት ከቻልን በልማቱም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ያሳየ ነው'' ሲልም ወጣቱ ተናግሯል።

በከተማው የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ከፈለኝ ለማ በበኩሉ ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እያስመዘገበች ያለችበት ወቅት ላይ መሆኗን አመልክቷል።

አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ የሀገርን ስም ሲያስጠሩና ባንዲራዋን ከፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሷል።

"በቡዳፔስት አትሌቶቻችን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያውያን ዳግም ኅብረትና አንድነት የሚያስገኘውን ውጤት እንድናጤን አድርጎናል" ብሏል ።

ኢትዮጵያውያን በየተሰማራንበት የሥራ መስኮች ጠንክረን ከሰራን ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ከአትሌቶቻቸን ተምረናል ሲልም ወጣት ከፈለኝ ተናግሯል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ከፍታ በሚያረጋግጡ የልማት ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ውጤት ለማምጣት ጠንክሬ እሰራለሁ ሲልም ገልጿል።

"የሀገራችን ባንዲራ በዓለም አቀፍ አደባባይ ሲውለበለብ ከመመልከት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም" ያለው ደግሞ በሐዲያ ዞን የሚሻ ወረዳ ነዋሪ ወጣት በረከት ዘውዱ ነው።

በአትሌቶቹ የተመዘገበው ስኬት ለኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ያለው ወጣቱ፣ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የቅንጅት ስራ ወሳኝ መሆኑን የአትሌቶቹ ውጤት አመላክቷል ሲል ተናግሯል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም