ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት የመገንባትና የማጠናቀቅ ተሞክሮ በሁሉም ስራዎች ላይ መንጸባረቅ አለበት-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 19/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት የመገንባትና የማጠናቀቅ ተሞክሮ በሁሉም ስራዎች ላይ መንጸባረቅ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።

በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአምባሳደሩ መኖሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ተመርቋል።

ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለውጡ ማግስት በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ያስተላለፉትን መመሪያ ተከትሎ የተጀመረ ሲሆን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት የመገንባትና የማጠናቀቅ ተመክሮ ከኢትዮጵያ ውጭም በሚገኙ የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ኢትዮጵያውያን ሥራዎች ላይ የሚንፀባረቅ ዕሴት መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ልዑካን ቡድናቸው በኤምባሲው ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም