ቀጥታ፡

በአቪዬሽን ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን ለመመከት አቅም እንደሚሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015(ኢዜአ)፦በአቪዬሽን ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን ለመመከት አቅም እንደሚሆኑ ተገለጸ።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ለ45 ቀናት ሥልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችን አስመርቋል፡፡

ሠልጣኞቹ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመለየትና ለመከላከል የሚያስችላቸውን መሠረታዊ ሥልጠና በፅንሰ-ሐሳብና በተግባር እንዲቀስሙ የተደረጉ መሆናቸውም ተገልጿል።

በሠልጣኞች የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በንቃት ሊቃኙ የሚገባቸው ወቅታዊና ተለዋዋጭ አደጋዎች ያሉበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እነዚህን አደጋዎች ቀድሞ መለየትና መከላከል መቻል ኢንዱስትሪው ሰላማዊና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታልም ብለዋል፡፡

በስኬታማነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞችና መሠረተ-ልማቶች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አመርቂ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተመራቂዎች የአየር መንገዱን ደኅንነት በማረጋገጥ ፈጣንና ለደንበኞቹ ምቹ አገልግሎት መሥጠት የሚችል እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።


 

ታላቅ ዓለም አቀፍ ስም ካተረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የምትሠሩ እንደመሆናችሁ በሥነ ምግባራችሁ ምስጉን፣ በሥራችሁ ታታሪና የተቋምን ስም በመልካም የምታስጠሩ መሆን ይጠበቅባችኋል ሲሉም አቶ ሲሳይ ቶላ ለተመራቂዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹና ደንበኞቹ እምነት የሚጥሉበት ሆኖ እንዲቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የጀመረውን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ አብራርተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤ሠልጣኞቹ የአቪዬሽን ዘርፉን ከማናቸውም አይነት አደጋ ለመጠበቅ የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ-ሐሳብ ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ተመራቂዎች የአገር አርማ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደኅንነቱ የተረጋገጠና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ የጎላ እንዲሆን ለማድረግ የወሰዱትን ሥልጠና በተግባር ላይ ማዋል ይገባቸዋል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ዴቪድ ፔኮስኬ በትናንትናው ዕለት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ዲጂታል ኤግዚቢሽን እንዲሁም በአገልግሎቱ ስር የሚገኘውን የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም