ቀጥታ፡

አርብቶአደርና ቆላማ አካባቢዎች በምግብ ራስን ለመቻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው-ሚኒስቴሩ

ድሬዳዋ ፣ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች  በምግብ ራስን ለመቻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የ2015 በጀት አመት የስራ እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2016 በጀት አመት እቅድ ውይይት በድሬደዋ ከተማ እየተካሄደ ነው ።

የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ  በውይይቱ  ላይ እንዳሉት  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎችና ሌሎች አጋሮች  ጋር በመሆን በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች በምግብ እራስን ለማቻል  የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።

“በአካባቢዎቹ የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ኃይል  በማቃናጀት  በምግብ እህል እራስን ለመቻል  የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው" ብለዋል።

በአርብቶ አደሩና ቆላማ አካባቢዎች በሚገኙ  ሰፊ ለም መሬቶችና የከርሰ ምድር ውሃ  በመጠቀም የተጀመረው የመስኖ ልማት ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

“ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዋና ጉዳይ ለሁለት መሠረታዊ ግቦች ነው” ያሉት ሚኒስትሯ  የመስኖ አቅምን በሚገባ ለይቶ የግብርና ዘርፍን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅና ወደ ዘመናዊነት ማሸጋገር አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ መሠረታዊ ተልእኮዎቹን  ለማሳካት በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ600 በላይ  የመስኖ መሠረተ ልማት ጥናትና የፕሮጀክቶች ዲዛይን ስራ ማጠናቀቁን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም የ1ሺህ 80 የመስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ በ251ሺህ  550 ሄክታር መሬት ለልማት ዝግጁ መደረጉን አመልክተዋል

ከዚሁ ጎን ለጎን 43ሺህ 700 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ የመስኖ መሰረተ ልማቶች ጥገና ስራም መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሯ አክለው በበጀት አመቱ የመስኖ ልማትን ለማሳለጥ ና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ 54ሺህ 515 የውሀ መሳቢያ ፓምፖች በፌደራልና በክልሎች አማካኝነት ተሰራጭተው 288ሺህ 796 ሄክታር መሬት ወደ ልማት ማስገባት መቻሉንም ጠቅሰዋል

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአርብቶ አደሮች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመታገዝና ከክልሎችና ሌሎች አጋሮች ጋር በመቀናጀት አርብቶ አደሮች የሚፈተኑበትን የድርቅና የጎርፍ አደጋ በመከላከል ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ በማቅረብ፣ የእንሰሳት መኖ ልማት ና የግጦሽ መሬት እንዲያገግም በተሰሩ ስራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሯ ጨምረው አስታውቀዋል

ኢትዮጵያ ያላትን የመስኖ ልማት አቅም በሚገባ ተንትኖ የሚያሳይ አገር አቀፍ ጥናት መካሄዱን የገለጹት ሚኒስትሯ በዚህም  በቀጣይ ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡና በትክክለኛ መረጃ ተንተርሶ በማልማት  ከተረጂነት ለመላቀቅና ወደ ውጭ አገራት በስፋትና በጥራት ምርት የመላክ ወሳኝ ስራ ለማሳካት ያስችላል “ ብለዋል።

በመጪዎቹ አመታት የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር የአርብቶአደር አካባቢ ፀጋዎችን በተገቢው መንገድ በማልማት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና መሠረታዊ ጥያቄ በመመለስ የአርብቶአደሩን ህይወት በመሠረታዊነት ለመለወጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።


 

 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  ሀርቢ ቡህ ወርሰሜ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ ወዲህ በድሬዳዋ አስተዳደር በአርብቶአደር አካባቢዎች የማህበረሰቡን  ህይወት ለማሻሻል እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ለበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።

ለሶስት ቀን በሚካሄደው መድረክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃና ቆላማ አካባቢና ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አባላት ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና የክልል የዘርፉ የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም