በቀጣይ 18 ወራት 47 አዲስ የአንድ መስኮት የግብዓት አቅርቦት ማዕከላትን ለማቋቋም ታቅዷል-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ 18 ወራት 47 አዲስ የአንድ መስኮት የግብዓት አቅርቦት ማዕከላትን ለማቋቋም ታቅዷል-ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ)፦ በቀጣይ 18 ወራት 47 አዲስ የአንድ መስኮት የግብዓት አቅርቦት ማዕከላት እንደሚቋቋሙ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የኮሜርሺያላይዜሽን ፕሮግራም ሲኒየር ዳይሬክተር ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ባለፉት አራት ዓመታት የግብርና ግብዓት የአንድ መስኮት አገልግሎት ሲሰራበት ቆይቷል።
እስካሁን በስድስት ክልሎች በሚገኙ 253 ወረዳዎች የግብርና ግብዓት አገልግሎት ማዕከላት ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
በቀጣይ 18 ወራት ተጨማሪ 47 አዲስ የአንድ መስኮት የግብዓት አቅርቦት ማዕከላትን በማቋቋም ማዕከላቱን 300 ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ይህም የአርሶ አደሮችን ገበያ መር የኩታገጠም እርሻ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
ማዕከላቱ አርሶ አደሮች ስለግብዓት አያያዝና አጠቃቀም በቂ መረጃና ዕውቀት እንዲያገኙ እንደሚያግዙ ገልፀው፤ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለማዕከላቱ የፋይናንስ፣ የስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
ምርጥ ዘር፣ አግሮ ኬሚካል፣ የእንስሳት ሕክምና መድኃኒት፣ መኖ፣ የእርሻ መሣሪያዎችና መሰል ግብዓቶችን በቀጣይነት በአንድ መስኮት የአገልግሎት ማዕከል ተደራጅተው እንዲቀጥሉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ምንም አይነት የፋይናንስ ድጋፍ ሳይደረግላቸው ግለሰቦች በራሳቸው አቅም በተቀመጠው መስፈርት መሰረት 95 የአንድ መስኮት አገልግሎት የወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ከአራት ዓመታት ወዲህ በተቋቋሙ ማዕከላት 9 ነጥብ 3 ሚለየን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች በማዕከላቱ ዋስትና ያላቸውን ሁሉንም ግብዓቶች ማግኘታቸው በኩታ ገጠም እርሻ ከራስ ፍጆታ ባለፈ ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የተለያዩ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋር አካላት የኢንስቲትዩቱን ዓላማ በተለያየ መንገድ እየደገፉ ይገኛሉ፡፡