ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የባለ ብዙ ወገን የኢኮኖሚ ልማት ትብብርን ለማስፋት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል- የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ክቡር ገና

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የባለ ብዙ ወገን የኢኮኖሚ ልማት ትብብርን ለማስፋት የላቀ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ክቡር ገና ገለጹ።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል፡፡

ይህም ከራሷ ባለፈ ለመላ አፍሪካዊያን ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በብሪክስ በሚኖራት ተሳትፎም ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄ እንዲኖርና የባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጎለብት እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በኢኮኖሚው መስክ የሚኖራት የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የባለብዙ ወገን የኢኮኖሚ ልማት ትብብርን ለማስፋት የሚያግዛት መሆኑን ገልጸዋል።

ብሪክስ ከተመሰረተ ጀምሮ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሌሎችም መስኮች በትብብርን ማዕከል ያደረጉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን አቅጣጫ ተልሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል።

የብሪክስ መስራች አገራት ከዓለም ኢኮኖሚ ያላቸው ድርሻ የላቀ መሆኑም አዲስ የተቀላቀሉት አባል አገራትን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፋይናነስ ትብብር ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘበ ተቋም ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰው፤ የብሪክስ አባል መሆኗም አዲስ የኢኮኖሚ ልማትና የፋይናንስ ትብብርን ለማስፋት ትልቅ አቅም መሆኑን አስረድተዋል።

"የብሪክስ ስብስብ ኢኮኖሚያዊ አቅም ቀላል አይደለም" የሚሉት ክቡር ገና፤ ተጨማሪ አባል አገራትን ማካተቱም በትብብር ላይ ለተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገት ፋይዳ አለው ብለዋል።

በገንዘብ ድጋፍ ረገድም የልማት ትብብርን ለማሳለጥ ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የልማት አቅም ያላቸው አገራት የብሪክስ አባል በመሆናቸውም ለጥምረቱ መጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት ጉባኤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የብሪክስ አባልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም