በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንዲጎለብት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሚና ትወጣለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንዲጎለብት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሚና ትወጣለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንዲጎለብት የሚጠበቅባትን ሚና ትወጣለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ ዓለምን እየፈተኑ ያሉ ችግሮች የባለ ብዙ ወገን ትብብር ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ትምህርት የሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡
የባለ ብዙ ወገን ትብብሮች አካታችና የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህም ፍትሃዊና ሰላም የሰፈነባት ዓለም ለመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ማበጀት አለብንም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፡፡
ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንደዲጎለብት ጽኑ አቋም እንዳላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብሪክስ በተደጋጋሚ ለሚነሳው አዲስና አካታች የትብብር ማዕቀፍ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሊግ አፍ ኔሽን እና አፍሪካ ህብረት መስራች አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ካላት የዳበረ የዲፕሎማሲ ልምድ አንጻር በባለብዙ ወገን የትብብር መድረኮች የምታደርገው ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት የያዘች አገር እንደመሆኗ የተሻለ የገበያ ፍላጎት፣ የፈጠራ ሃሳብና አምራች ኃይል ተደራሽ በማድርግ ትብብሮች ይበልጥ እንዲጎለብቱ ከፍተኛ ሚና አላት ብለዋል፡፡
ከጂኦ-ፖለቲካ አንጻርም አፍሪካን፣ ከመካከለኛው ምስራቅና እስያ ጋር በማገናኘት የትስስር ማዕከል እንድምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመንገድ፣ ቴሌኮምና ሌሎችም ዘርፎች እያከናወነች ያለው ስራም ከቀጣናው ባለፈ አፍሪካን ለማስተሳሰር ያላትን አቅም እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት የመሆን ትልም በመያዝ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የሚደገፍ መሆኑ ደግሞ ብዝሃ እና ችግሮችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም እየተፈተነ ያለበትን የአየር ጠባይ ለውጥ በመከላከል በኩል ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች መሆኑን ጠቅሰው፤ ለእዚህም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የረዥም ዘመን ታሪክ እንዲሁም የዳበረ የሁለትዮሸና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ተሳትፎና ልምድ አንጻር ከብሪክስ ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረኮች አካታችነት እንዲጎለብት ወሳኝ ሚና እንደምታበረክት ተናግረዋል፡፡
በብሪክስ በሚኖራት ተሳትፎም ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄ እንዲኖር ከመስራት ባለፈ መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን የሚጠበቅባትን ሚና እንደምትወጣ አረጋግጠዋል፡፡