የፌደራል ተቋማት በሱማሌ ክልል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል ተቋማት በሱማሌ ክልል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ
ጂግጅጋ ፣ነሀሴ 18/2015 (ኢዜአ):-የፌዴራል ተቋማት በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በክልሉ ያከናወኗቸው የልማት ሥራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ተናገሩ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በተጠሪ ተቋማት በሶማሌ ክልል ደረጃ የሚከናወኑ የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራዎች የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በሀርቲሼክ ከተማ ተካሂዷል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድና የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲሆኑ በመርሀግብሩ ላይም የክልልና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎችና የከተማው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በሀርቲሼክ ከተማ በሚገኘው ሼህ አህመድ ቦን አንደኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ግቢ ችግኝ በመትከል መርሀግብሩ የተጀመረ ሲሆን፣ ለ1 ሺህ ተማሪዎችም የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
ከእዚህ በተጨማሪ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ስምንት የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት በአዲስ የመገንባት ሥራ እንደሚከናወን ተመላክቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትርና ተጠሪ ተቋማቱ ወደህዝቡ ወርደው በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እያከናወኗቸው ያሉ ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግሮች የሚያቃልሉ ናቸው።
በክልሉ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በፌዴራል ተቋማት የሚደረጉ ድጋፎች እነስተኛ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙስጠፌ፣ ከለውጡ ወዲህ የተለያዩ የፌደራል ተቋማት በክልሉ ልማቶችን በማከናወን እየደገፉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ተጠሪ ተቋማት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከአራንጓዴ አሻራ ሥራ ጎን ለጎን አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች ማከናወናቸውንም ገልጸዋል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የተጀመሩ ሥራዎች አርዓያነት ያላቸው በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የፌዴራል ተቋማት ክልሉን በልማት ለማገዝ እያደረጉት ላለው ሥራ በህዝብ ስም አመስግነው፣ ልማቶቹ ህዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ዋና ዓላማ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በክልሉ አቅም ሲሰሩ የቆዩ የልማት ሥራዎችን መደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
"በበጎ ፍቃድ ሥራዎቹ በዋናነት የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ወጪ ቆጣቢ የግንባታ ሥራዎች ከማከናወን ባለፈ ለወጣቶች የግንባታ ቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርና የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል" ብለዋል።
በዛሬው እለትም ለ1 ሺህ ወጣቶች ለመጨው የትምህርት ዘመን የሚያገለግሉ የትምህርት ቁሶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና የወላጆቻቸውን የትምህርት ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ከለውጡ ወዲህ በግብርና፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ላከናወናቸው ሥራዎች ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩና እና በተጠሪ ተቋማቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በፋፈን ዞን ቀብሪበያህ ወረዳ ሀርቲሼህ እና ቀብሪበያህ ከተማ ያሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።
የአመራር አካላቱ በሀርትሼክ ከተማ በሚገኘው ሼህ አህመድ ቦን የአንደኛና መለስተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አራንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።