በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ እንቅስቃሴዎችን በማስወገድ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር ይሰራል... ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ እንቅስቃሴዎችን በማስወገድ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር ይሰራል... ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ)፦በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ እንቅስቃሴዎችን በማስወገድ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት የመፍጠር ስራ በልዩ ትኩረት የሚከናወን መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
“ሁለንተናዊ ርብርብ ለትምህርት ተቋማት ደረጃ መሻሻል” በሚል መሪ ሃሳብ 30ኛው አመታዊው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የትውልድ ግንባታ ማእከል የሆኑት ትምህርት ቤቶች ጥሩ የመማሪያ ቦታ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ እንቅስቃሴዎችን በማስወገድ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት የመፍጠር ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ሲሉ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ተግባር ስኬታማ ለማድረግ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቋማቱን ደረጃ ማሻሻልና መምህራንን የማሰልጠን ተግባር ቁልፍ ስራ ሆኖ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በመላ ሀገሪቱ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የዜጎች ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ በመዲናዋ የትምህርት ቤቶችን ውስጣዊ አሰራር ለማስተካከል የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዕውቀት፣ በክህሎትና አመለካከት የተለወጠ የትምህርት አመራር፣ መምህራንና ባለሙያዎች እንዲኖሩ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሔደው ጉባኤ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አፈፃፀም ግምገማ የሚካሔድ ሲሆን የ2016 ዓ.ም መሪ እቅድ ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ይሆናል።