የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ማግኘቱ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገበ ላለው ስኬት ማሳያ ነው-ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ማግኘቱ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገበ ላለው ስኬት ማሳያ ነው-ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ማግኘቱ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገበ ላለው ስኬት ማሳያ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ ገለጹ።
በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የአባል አገራት መሪዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
በጉባኤውም ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል አገራት ሆነዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉን ኢዜአ አነጋግሯል።
ፕሮፌሰር ብሩክ በማብራሪያቸው ለረጅም ዓመታት ዓለም ከሁለትና ሶስት በማይበልጡ አገራት የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ስትመራ መቆየቷን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አገራት ጥምረት እየፈጠሩ የበላይነቱን ተመጣጣኝ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህ ዓላማ ተብለው ከተፈጠሩ ጥምረቶች ውስጥ ደግሞ በፈረንጆቹ 2009 የተመሰረተው የብሪክስ አባል አገራት ጥምረት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የብሪክስ አባል አገራት ከፖለቲካ ይልቅ ጥምረታቸውን የኢኮኖሚ ትብብር ላይ ያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ይህም እየዋዠቀ ያለውን የአለም ኢኮኖሚ ሚዛን የሚያስጠብቅ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ በሁሉም ዘርፍ መልካም እድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን ፕሮፌሰር ብሩክ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ማግኘቱ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገበ ላለው ስኬት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እኤአ በ2014 የብሪክስ አገራት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሃብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለውን "ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ" ወይም ብሪክስ ባንክ በ250 ቢሊዮን ዶላር አቋቁመዋል።
የባንኩ መቋቋም ትኩረት ያደረገው በኃይል፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ በውሃ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በማኅበራዊ ልማት ላይ መሆኑም ይታወቃል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በ10 ዓመታት ውስጥ እደርስበታለሁ ብላ ላስቀመጠችው የልማት እቅድ መሳካት የሚያግዝ መሆኑንም ፕሮፌሰር ብሩክ ገልጸዋል።
የብሪክስ አባል አገራት አጠቃላይ ገቢ 26 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከዓለም ምጣኔ ሃብት 26 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።