ቀጥታ፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያካሄዳቸው የተሳታፊ ልየታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ)፦የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያካሄዳቸው የተሳታፊ ልየታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ በአጀንዳ ማሰባሠብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ አካላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት በዛሬው እለት ስልጠና መስጠት ጀመሯል።

በመርሃ-ግብሩ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች፤ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበራት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ስልጠናው ለቀጣዮቹ ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የአገራዊ ምክክሩ ምንነት፣ አካሄድ ፣የሚያስገኘው ውጤት እና የልየታ ስነዘዴ ላይ እንደሚያተኩር ተመላክቷል።


 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚሁ ወቅት ኮሚሽኑ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በተፈጠሩ ልዩነቶች በውይይት ዘላቂ ዕልባት እንዲያገኙ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ትብብር፣ ሕጋዊነትና ተዓማኒነትን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ ወቅታዊ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና ማህበራዊ መደላደል በማመቻቸት ታላላቅ አገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚካሄድ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ወሳኝ ተግባር በአግባቡ ለመፈጸም የሚረዳ የተሳታፊ ልየታ የአሰራር ስርአት በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ባለውም ሂደት በሲዳማ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስኬታማ የሆነ የተሳታፊዎች ልየታ ተከናውኗል ብለዋል።


 

እንዲሁም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሳታፊ ልየታው በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሂደቱም ኮሚሽኑ መርሆዎቹን መሰረት በማድረግ የለያቸው ተባባሪ አካላት ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚያካሂደው የተሳታፊ ልየታ ስራ ስኬታማ እንዲሆን በስልጠናው የሚሳተፉ ተባባሪ አካላት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

ልየታው በከተማ አስተዳደሩ ባሉት 11 ክፍለ ከተሞች እና 119 ወረዳዎች እንደሚካሄድ ገለጸው ተባባሪ አካላት ልየታውን በገለልተኝነት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በሚያሳትፍ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችም ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም