የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በ2015 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በ2015 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታወቀ
የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በ2015 በጀት ዓመት ደንበኞች ላይ ለደረሰው ጉዳት ለቀረቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈፀሙን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዓመታዊ የሥራ አመራር ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሶሰት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የዘንደሮው በጀት አመት ሥራዎች ላይ ውይይት ይደረጋል።
የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ፤ ድርጅቱ በ2015 ዓ.ም ውል በመሸጥ ወይንም ሽፋን በመስጠት 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ አስገብቷል ብለዋል።
ከተስብሳቢ አረቦን አኳያም በበጀት ዓመቱ 85 በመቶ ለመሰብሰብ ታቅዶ 89 በመቶ መሰብሳቡን ጠቅሰዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ደንበኞች ላይ ለደረሰው ጉዳት በንብረትና በሕጋዊ ኃላፊነት ምክንያት ለቀረቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈፀሙንም ገልጸዋል።
ድርጅቱ አረቦን በመሰብሰብ፣ ካሳ በመክፈል ከውል ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በማከናወን ከታክስ በፊት ገቢ ለማስገባት የታቀደውን 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ ተግኝቷል ብለዋል።
በዓመቱ በአገሪቷ የሚገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ የልማት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወኑ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ድርጅቱ በማህበራዊ ሃላፊነትም የላቀ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች 28 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ መሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የዳታ ማዕከሉን እንደ አዲስ ለመገንባትና ኔትወርክ ማሻሻያ ለማድረግ ውል የፈረመ ሲሆን የሚጠቀምባቸውን መተግበሪያዎች ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።