የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ የሚኒስቴሩን የ2016 በጀት ዓመት እቅድና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ ያጠናከረ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅና ባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኝኑነት ወደ ላቀ ትብብር ያሸጋገረ ምዕራፍ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን ያስታወሱት አምባሳደር መለስ፤ ከስምምነቶቹ መካከል የኢኮኖሚ፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የግብርና እና ትምህርት ይገኙበታል ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥና በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ በጋራ የመስራት የትብብር ፍላጎት እንዳለም በሁለቱም አገራት መሪዎች መገለጹን አንስተዋል።
አምባሳደር መለስ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል የሆነችው አንዱን ጎራ ትቶ ሌላ ጎራ ፍለጋ አለመሆኑን በማብራራት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ገለልተኝነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የባለብዙ ወገን አራማጅ ሀገር በመሆኗ የገንቢ ገለልተኝነት የዲፕሎማሲ አቋም አንዳላትም አስረድተዋል።
በ2016 በጀት ዓመትም የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት በመፍጠር አሳታፊ የዲፕሎማሲ ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።