የክልሉን አቅም አሟጦ በመጠቀም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል--ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን አቅም አሟጦ በመጠቀም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል--ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ ፣ነሀሴ 18/2015 (ኢዜአ):- የክልሉን አቅም አሟጦ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለማምጣትና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በቅርቡ የተመሰረተውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚመሩ አመራሮች ተመድበው ሥራ ጀምረዋል።
በክላስተር አወቃቀር የተደራጀው ክልሉ ስድስት መቀመጫ ከተማዎችን በመምረጥ በዋናነት የመንግስትና የህዝብ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ቢሮዎችን የማደራጀት፣ የሰው ሃይል የመመደብና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።
ቀድሞ የነበረው ክልል ለአንዳንድ አካባቢዎች ርቀት ስለነበረው የመንግሥት አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ክፍተት ከመኖሩ ባለፈ የህዝብን ተጠቃሚነትና ወቅታዊ ፍላጎትን ያላማከለ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር፣ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላትና ባለቤትነቱን በተጨባጭ ለማረጋገጥ ክልሉ መመስረቱንም አቶ ጥላሁን አስታውቀዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ ለክልሉ በመቀመጫነት የተመረጡት ከተሞች ለህዝቡ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመዘርጋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈም የሚያስችል ነው።
ይህም ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ፣ የከተሞችም እድገት የተመጣጠነና የተቀራረበ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
ክልሉ የተፈጥሮ ጸጋን የተጎናጸፈ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ለሜካናይዜሽን ግብርና ልማት አመቺ የሆነ ሰፊ ያልታረሰ መሬት፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ ሰፊ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ ሀብት ባለቤት መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በክልሉ በሁሉም መስክ በተነደፉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅዶች ፈጣን ልማት ለማረጋገጥና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።
ይህንን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የባለሀብቱንና የህዝቡን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ አቅም አሟጦ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለማምጣትና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ክልሉ የገቢ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከተለያዩ አካላት ጋር በመምከር የገቢ አቅምን ከፍ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በቀጣይ በክልሉ ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም አካላት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።