ቀጥታ፡

የግል ባለሃብቶች በእንፋሎት ኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶች ተዘጋጅተዋል...የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፡- የግል ባለሃብቶች በእንፋሎት ኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶች ና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።

የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ከከርሰምድር የሚወጣ እንፋሎትን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚለወጥበት ሂደት ሲሆን ኢትዮጵያ ከእንፋሎት 10 ሺህ ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት በጥናት ተለይቷል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ  በዘርፉ ያላትን አቅም ጥቅም ላይ እያዋለች አለመሆኑ እሙን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ለእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ካላት አቅም አንጻር ጥቅም ላይ የዋለው እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ወደ 7 ነጥብ 3 ሜጋ ዋት ሲያመነጭ የነበረው የአሉቶ ላንጋኖ አንዱ በዘርፉ የለማ ማመንጫ ጣቢያ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የአሉቶ ላንጋኖን ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 70 ሜጋዋት ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ በመሆኑ አሁን ላይ የኃይል ማመንጨት ስራውን እያከናወነ አለመሆኑንም ገልፀዋል።

ለዚህም ወደ አስር ጉድጓድ መቆፈሩን ጠቅሰው፤፤ ከእነዚህም ስድስቱ ጉድጓዶች የሚፈለገውን ያህል እንፋሎት ማውጣት ስለመቻላቸው ፍተሻ ተደርጎ 25 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል መረጋገጡን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በግል ባለሃብቶች እየለማ  መሆኑን ተመናግረዋል፡፡

የስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሆኑ የኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የከርሰምድር እንፋሎት ለማመንጨት የሚያስችሉ ጥናቶቸ መካሄዳቸውንም ተናግረዋል።

ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የሰለጠነ ኃይል እንደሚፈልግ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ዘርፉ በሚገባ እንዳይለማ ውስንነት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም  የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ከውጭ ከመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በማቀናጀት ልምድ የሚቀስሙበት ሁኔታ መመቻቸቱን  አንስተዋል።

በሙያው የካበተ ልምድ ካላቸው አገሮች ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የግል ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል የህግ ማእቀፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶች  መዘጋጀታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኃይል ማምረት ስብጥር ውስጥ ከውሃ የሚገኘው ኃይል የ96 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ በቀጣይ 10 ዓመታት የሃይል አማራጮችን በማስፋት ዘርፉ በውሃ ላይ ያለውን ጥገኝነት ወደ 75 በመቶ ዝቅ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም