በተያዘው በጀት ዓመት የላቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመስረትና አጋርነትን ለማስፋት ይሰራል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው በጀት ዓመት የላቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመስረትና አጋርነትን ለማስፋት ይሰራል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2016 በጀት ዓመት የላቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመስረትና አጋርነትን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት ከድህረ-ጦርነት በኋላ የከረሩ አቋሞችን የማለዘብ እንዲሁም ወዳጆችን የማስገንዘብና የማስረዳት ስራዎችን በማከናወን ዲፕሎማሲውን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት የመመለስ ስኬታማ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪና ተደማጭ በመሆን ተገቢው ቦታዋን እንድትይዝና ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከአገራት ጋር ለሚኖራት ፈርጀ-ብዙ ግንኙነት የዲፕሎማሲ መርሆችን ትከተላለች ብለዋል።
በጎረቤት አገሮችና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ስራዎችን ታከናውናለች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
ከባህረ ሰላጤና ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በውጭ አገር የስራ ስምሪት መስክ እንዲሰፋ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በንቃት ተሳታፊ መሆን በዚህም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ሕብረትና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ላይ ያላትን የባለብዙ ወገን ተሳትፎ በማጠናከር ለልማቷ የሚሆኑ ድጋፎችን ለማግኘት ትሰራለች ብለዋል።
የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ በማጎልበት የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን እንዲፈታ መስራት ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ነው አምባሳደር መለስ ያብራሩት።
ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሰፋ፣ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የመተማመን መንፈስ የበለጠ እንዲጎለበት፣ ከእስያ ፓሲፊክና ከደቡብ አሜሪካ አገራት ጋር ያሉንን ፈርጀ ብዙ የዲፕሎማሲ አቅሞችን የመጠቀም ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ የመደበኛ ዲፕሎማቶች ስራ ብቻ ባለመሆኑ በአሳታፊና አካታች በሆነ ዘርፈ ብዙ አካሄዶቸን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሞችን በሙሉ አቅም ለመጠቀም በአቪዬሽን፣ በስፖርት፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በኪነ-ጥበብ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የአገሪቱን አቅም የሚያሳድጉ የዲፕሎማሲ አካሄዶችን በመከተል እንደምትሰራ አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት፤ የውስጥ አቅምን ለማጠናከር ለሙያዊ ክህሎትና ብቃት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።
አምባሳደር መለስ በ2015 በጀት ዓመት ዲፕሎማሲውን ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲመለስ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በ2016 በጀት ዓመት በተሻለ ትጋት የላቀ ውጤትና አጋርነት ለማስመዝገብ ተቋሙ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።