ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2013 ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 24 ሺህ ተማሪዎችን በመቀበልና በማስተማር ላይ ናቸው-ትምህርት ሚኒስቴር

 አዲስ አበባ  ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2013 ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 24 ሺህ ተማሪዎችን በመቀበልና በማስተማር ላይ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የአስተዳደርና መሰረተ ልማተ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን አብርሃ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከ2013 ሰኔ 21 ቀን ጀምሮ በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት የከፍተኛ ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም በወቅቱ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሲማሩ ከነበሩ 46 ሺህ ተማሪዎች መካከል 22 ሺህ የሚሆኑትን በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ በማድረግ ከፊሉ መመረቃቸውን ተናግረዋል።

የተወሰኑ ተማሪዎችም በተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት  ላይ እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።

በጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰሜኑ ጦርነት በውይይት በመፈታቱ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የዝግጅት ስራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን ሁኔታ በመዳሰስ እና ከአመራሮቻቸው ጋር በመወያየት የተማሪ ምገባ፣ ማስተማሪያ፣ ማደሪያና የህክምና መሰረተ ልማቶችን ምቹነት የማረጋገጥና የማሟላት ስራዎችን ባለፉት ስድስት ወራት ስለመከናወናቸውም አብራርተዋል።

በዚህም በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2013 ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 24 ሺህ ተማሪዎችን በመቀበልና በማስተማር ላይ መሆናቸውን ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን የተቀበሉ እንዳሉ ጠቅሰው፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲም በ2013 ዓ.ም ተመራቂ የነበሩ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን በቀጣይ ሌሎችንም ለመቀበል ተዘጋጅቷል ብለዋል።

መምህራንና ተማሪዎችም የስነልቦና ማገገሚያ ስልጠናዎች እንዲያገኙ፣ ተከታታይ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አዳዲስ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ካላቸውም በቀጣይ የሚወሰን ይሆናል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም