የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል ለአገልግሎት በቃ

ሆሳዕና፣ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ)- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት ጀመረ ።
ማእከሉን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው።
የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደገለ ደስታ በምረቃ ስነ ስርአት ላይ እንዳስታወቁት ማእከሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።
ማእከሉ ለመማር ማስተማር የሚያመች የገጽ ለገጽ ማስተማሪያና የቪዲዮ ኮንፈረንስ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ሌሎች በኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ክፍሎች እንዳሉት ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ይህም የመማር ማስተማር ሥራ ለማቀላጠፍና ተደራሽ ለማድረግ፣ ዲጂታል ቤተ መጻህፍት ለተማሪዎች ምቹና ቀልጣፋ በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።
በምረቃው ስነ ስርአት ላይ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና መምህራን ተገኝተዋል።