ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 125 ከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል-አገልግሎቱ

አዳማ፣ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ ):-  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  125 ከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ የ2015 በጀት አመት የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2016 በጀት አመት እቅድ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ በተጠናቀቀው በጀት አመት 125 ከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ።

ከዚሁ ጎን ለጎን ለ353ሺህ 144 አዲስ ደንበኞች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን  ተናግረዋል።

በጀት ዓመቱ ከአገልግሎት ከ35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል  የተጎዱ የሀይል የማሰራጫ መስመሮችን ጠግኖ ወደ ስራ የማስገባት ተግባር መከናወኑን አመልክተዋል ።

አገልግሎቱ ደንበኛ ተኮር የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በሚሰጠው አገልግሎት ዙሪያ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት የደንበኞች ዕርካታ 60 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የሃይል ማሰራጫ መሰረተ ልማት ደረጃ ማሻሻልና ማዘመን፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት ዲጂታል ማድረግ ፣አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም መገንባትና የሰው ሃይል የመፈፀምና ማስፈፀም አቅም ግንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የደንበኞች ግንኙነት ስርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና አሰራር ማሻሻል ላይም ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ የሃይል መቆራረጥና መዋዠቅ፣ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በወቅቱ ያለመጠናቀቅ እንዲሁም በአንዳንድ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ጉድለቶች ከበጀት አመቱ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተያዘው 2016 በጀት አመት ተግዳሮቶችን በመፍታት የደንበኞችን ዕርካታ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

በመድረኩ ላይ  ከሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ የዘርፉ የስራ አመራሮችና ሙያተኞች እየተሳተፉ ነው ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም