ቀጥታ፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቢሮዎች በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ተደራጅተው ወደ ተሟላ አገልግሎት ይገባሉ-ርዕሰ-መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ የአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቢሮዎች በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ተደራጅተው ወደ ተሟላ አገልግሎት እንደሚገቡ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

አዲስ የተመሰረተው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ" ጠንካራ ክልል መፍጠር" በሚል መሪ ሀሳብ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር  አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በቀጣይ ሶስት ወራት የሚተገበሩ የመቶ ቀናት ዕቅድ መዘጋጀቱንና ምክክር እንደሚደረግበት ገልፀዋል።

የክልል ምስረታው ለረጅም ጊዜ ሲነሱ የቆዩ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በህዝቡ ውሳኔ የተመለሱበት መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ከመቶ ቀናት ዕቅዶች መካከልም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የክልል ቢሮዎችን ወደ ተሟላ አገልግሎት ማስገባት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በተደራጀ መንገድ ስራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

በአዲሱ ክልል በሦስት ወራት ውስጥ ከህዝብ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ እንዲሁም የጋራ መግባባት የሚፈጠርባቸው መድረኮች እንደሚካሄዱም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም