በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ሊጠናከር ይገባል -የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ሊጠናከር ይገባል -የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ)፡- በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ባለድርሻ ተቋማት ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ከተሠማሩ ማህበራትጋር "የቱሪዝም መሪዎች ወግ" በሚል በየወሩ የሚካሄደውን የውይይት መድረክ ዛሬ አስጀምሯል፡፡
ውይይቱም በዋናነት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በትብበር በመቅረፍ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው ተብሏል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታሰብ ስዩም በዚሁ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ተገቢውን ፕሮሞሽን አለመስራት በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ወርሃዊ የውይይት መድረኩም በዚህ ረገድ የተሻሉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያዊነት ቀለም የጠበቀ አገልግሎትን በማላቅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅት መጠናከር እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
"የቱሪዝም መሪዎች ወግ" በሚል በቀጣይነት በሚካሄደው የውይይት መድረክም ተመራማሪዎች፣ ባለሙያች፣ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች፣ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
በዛሬው የውይይት መድረክ ከተሳተፉት መካከል የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት ክብሮም ተስፋዬ፤ በቱሪዝም ዘርፉ ውስጥ የባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ድርጅት ማህበር የተወከሉት ናሆም አድማሱ በበኩላቸው የተሻሉ የሚባሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶችን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በባለድርሻ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ ማድርግ እንደሚያስፈልግም እንዲሁ፡፡