የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በትግራይ ክልል ለእግር ኳስ አሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በትግራይ ክልል ለእግር ኳስ አሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ
መቀሌ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በትግራይ ክልል ለ60 የእግር ኳስ አሰልጣኞች "በካፍ ዲ ላይሰንስ" የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
በፌደሬሽኑ ኤሊት ኢንስትራክተር አብራሃም መብራቱ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ስልጠናው ሲጀመር እንዳሉት ስልጠናው በክልሉ በዘርፉ ያለውን ክፍተት በመሙላት የስፖርቱን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅም ይፈጥራል።
በየደረጃው የሚሰጠው ስልጠና ሰልጣኖች ከክልልና ከሀገር ውስጥ ባለፈ በአህጉር ደረጃ አሰልጣኝ ለመሆን የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ስልጠናው ከንድፈሳብ በተጨማሪ በሜዳ ላይ በተግባር የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።
ስልጠናው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀና ለተከታታይ 11 ቀናት የሚሰጥ መሆኑን ኤሊት ኢንስትራክተር አብራሃም መብራቱ አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእግር ኳስ ፈደሬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞጎስ ተፈራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈደሬሽን የክልሉን የስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ አመስግነዋል ።