የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተሁለደሬ ወረዳ የአርሶ አደሮችን የሰብል ማሳ ከአረም የማፅዳት ስራ አከናወኑ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተሁለደሬ ወረዳ የአርሶ አደሮችን የሰብል ማሳ ከአረም የማፅዳት ስራ አከናወኑ
ደሴ፤ ነሐሴ 17 /2015፡-የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህግን ከማስከበር በተጓዳኝ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የሰብል ማሳ ከአረም የማፅዳት ስራ እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ ፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የምስራቅ አማራ ሪጅን ኮማንድ ፖስት የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መከላከያ ሰራዊቱ የሀገር ዳር ድንበርና ህግን ከማስከበር ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
''ለስራ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሁሉ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራት፣ የአርሶ አደሮችን ሰብል በማረም፣ የደረሰ ሰብል በማጨድና በሌሎችም የልማት ስራዎች በመሳተፍ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል" ብለዋል፡፡
ዛሬም በተሁለደሬ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ከአረም ማፅዳታቸው የዚሁ አካል ነው ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ፤ ሰብሉ ሲደርስም ለማጨድና ለመውቃት ሰራዊቱ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞንም ከቦረና ሳይንት መገንጠያ-ሳይንት አጅባርና ዴንሳ 23 ኬሎ ሜትር ጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ለመቀየርና በሳይንት ወረዳ አንድ ትምህርት ቤት በ400 ሺህ ብር ደረጃውን ለማሻሻል ማቀዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ህብረተሰቡም ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ በተለያየ ዓይነት ድጋፉን በተግባር ማረጋገጡ የበለጠ እንድንሰራ ከማድረጉ ባለፈ የህግ ማስከበር ስራችን ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ከሰራዊቱ አባላት መካከል ወታደር ትብለጥ ጌታቸው በሰጠችው አስተያየት ''ሰራዊታችን ከተለያዩ ብሔር በሔረሰቦች የተውጣጣን የኢትዮጵያ የህዝብ ልጅ በመሆናችን ህግ ከማስከበሩ ጎን ለጎን ህብረተሰቡን በማገልገል ህዝባዊነታችን በተግባር እያረጋገጥን ነው'' ብላለች፡፡
''ህዝባችን ከጎናችን ተሰልፎ ሁለተናዊ ድጋፍ በማድረግ ሞራልና ብርታት እየሆነን ነው፤ እኛም ለህዝባችንና ለሀገራችን በጉልበታችን ከማገልገል ባለፈ መስዋት ለመሆኑ ቁርጠኛ ነን'' ስትል ገልጻለች፡፡
ዛሬ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን የሰብል ማሳ ከአረም ማጽዳታቸውንና በሌሎች ወረዳዎችም ከአረም ስራ ባሻገር ሰብሉ ሲደርስ ለማጨድና ለመውቃትም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡
''ህግ ለማስከበር በሄድንበት አካባቢ ሁሉ ህዝባችንን በጉልበታችን ጭምር በማገልገል ፍቅራችንን በተግባር እያሳየን ነው'' ያሉት ደግሞ ሺአለቃ መላኩ ቶላ ናቸው፡፡
ህብረተሰቡም ከጎናቸው ተሰልፎ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ በበኩላቸው ፤መከላከያ ሰራዊቱ ህግ ከማስከበር ባለፈ ህዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የአቅመ ደካሞችን ሰብል በማረምና በሌሎችም የግብርና ስራዎች እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ ሰብሉን ከአረምና ከተባይ እንዲከላከልም አሳስበዋል፡፡
በተሁለደሬ ወረዳ የ08 ቀበሌ አርሶ አደር መሃመድ አሊ በሰጡት አስተያየት ፤በመኽር ወቅቱ በግማሽ ሄክታር መሬት ያለሙት የስንዴና ጤፍ ሰብል በህመም ምክንያት ሳይታረም መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዛሬ መከላከያ ሰራዊት ሰብሉን በማረሙ መደሰታቸውንና በዚህም ሰራዊቱ ምንጊዜም የህዝብ ልጅ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
በአረም ስራው ከመከላከያ ስራዊቱ በተጨማሪ የደቡብ ወሎ ዞንና የተሁለደሬ ወረዳ አመራሮችም ተሳትፈዋል፡፡