ቀጥታ፡

 በሰሜንና በምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች የዝናቡ መጠንና ስርጭት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦በቀጣዩ አስር ቀናት በሰሜንና በምዕራብ የአገሪቱ  አካባቢዎች የዝናብ መጠንና ስርጭት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት 10 ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የአየር ፀባይ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ልኳል።

ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ ፣በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች  የሚገኙ ቦታዎች የተሻለ የዝናብ  ስርጭት እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም የወለጋና የሸዋ ዞኖች በጅማ ሆሮጉድሩ ኢሉአባቦር  አርሲ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች  ፣ ሁሉም የአማራ ክልል ዞኖች፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ዞኖች እና አዲስ አበባ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ አስታውቋል።

ጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞን፣ የትግራይ ክልል ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 1 እና 4፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ፣ሸካና ከፋ ዞኖች፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ሀድያ ከንባታ፣ ጉራጌ፣ የጌዲኦ የስልጤና የየም ዞኖች ፣የሲዳማ ክልል ዞኖች ላይ ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ሁኔታን የሚያስተናግዱ መሆናቸውን መግለጫው አመላክቷል።

የሰሜን ምዕራብና የምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተጠናከረ የደመና ክምችት ሳቢያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱ ተገልጿል።

በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች  ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በሰሜንና በምዕራብ አጋማሽ በሚገኙ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተለያዩ የግብርና ምርቶችና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል።

በሰብል ማካከል የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን  በመስራትና በመንገድ አካባቢ የተሰሩ ቦዮችን በመጠረግ ህብረተሰቡ እራሱን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቅ መግለጫው አመልክቷል።

በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ በሰሜን በሰሜን ምዕራብ በምዕራብ በደቡብ ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ የውሀ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም