የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት በአፍሪካ ስመጥር የጥናት እና የማማከር ተቋም እንዲሆን እየተሰራ ነው-አቶ አከሊሉ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት በአፍሪካ ስመጥር የጥናት እና የማማከር ተቋም እንዲሆን እየተሰራ ነው-አቶ አከሊሉ ታደሰ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ)፡- የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት በአፍሪካ ስመጥር የጥናት እና የማማከር ተቋም እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አገልግሎቱ ላለፉት 40 ዓመታት የማማከርና የማሰልጠን ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች በሚመሰረቱበት ወቅት እውቀትና አዋጭነታቸው በጥናት የተረጋገጠ እንዲሆን ሰፋፊ ስራዎችን መስራታቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም እንደ ሙገር ሲሚንቶ፣ አዋሳ ጨርቃጨርቅና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን አጠቃላይ ግንባታ ላይ ጉልህ አሻራ ማሳረፉን ተናግረዋል።
እንዲሁም የኢንዱስትሪዎችን መዋቅር የመስራት እንዲሁም የማማከር እና ስልጠናዎችን በመስጠት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት 40 ዓመታት አገልግሎቱ ከ600 በላይ ትላልቅ ኩባንያዎችንም ማዋቀር መቻሉንም ነው የተናገሩት።
ተቋሙ አሁን ላይ አለም ወደደረሰበት ደረጃ ማደግ እንዳለበት በመታመኑ፤ ከኮርፖሬሽኑ 9 የሪፎርም ስራዎች መካከል አንዱ ይህን ተቋም ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ተቋሙ በአፍሪካ ስመጥር የማማከር እና የስልጠና ተቋም እንዲሆን በርካታ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከሰው ሀይል ጀምሮ በየደረጃው ተቋሙን በልምድም በእውቀትም ማገዝ የሚችሉ አመራሮች ምደባ መካሄዱን ጠቁመዋል።
እንዲሁም መዋቅራዊ ጥናቱን በመከለስ በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪ የማማከር እና የማሰልጠኛ ተቋም እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።
በጊዜያዊነት የአገልግሎቱን የሪፎርም ስራዎች በመምራት ላይ የሚገኙት አቶ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው በቀጣይ አዋጭነትን ብቻ ሳይሆን እስከ ፕሮጀክቶቹ መጨረሻ ድረስ የመደገፍ ስራዎችን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተለይም ባንኮች ለተበላሸ ብድር እንዳይጋለጡ ፋይናንስ የሚያደርጓቸው ፕሮጀክቶች የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በቀጣይም በዘርፉ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።