ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ኢቶ ታካኮ - ኢዜአ አማርኛ
ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ኢቶ ታካኮ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ለኢዜአ እንደገለጹት ጃፓንና ኢትዮጵያ ያላቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በተለይም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ተከትሎ በርካታ የጃፓን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ለማሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
በተጓዳኝም ጃፓን በኢትዮጵያ የግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ ጃፓን በመስኩ ያካበተችውን ልምድ ለማካፈል እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
ጃፓን በዓለም አቀፍ ደረጃ አደጋ የደቀነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የምትሰራውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያና የጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1930 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።