ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነገ በሚጀመረው የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ አመራሮች ዛሬ በሰጡት መግለጫ በመዲናዋ ከነገ ጀምሮ ለሚካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። 

በሂደቱ የሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የመምህራን ማህበር፣ የእድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የወረዳ አስተዳደሮች ትብብር እንዲያደርጉ መመረጣቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ገልጸዋል።

ለተባባሪ አካላት ስልጠና በመስጠት የልየታ ሂደቱን እንዲያስተባብሩ እና ገለልተኛነቱን፣ አሳታፊነቱን ግልፅነቱንና አካታችነቱን እንዲከታተሉ ይደረጋል ብለዋል።

የተሳታፊ ልየታ ስራው በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ወረዳዎች እንደሚከናወን ያነሱት ምክትል ዋና ከሚሽነር ሂሩት፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የሃይማኖትና የማህበረሰብ መሪዎች፣ ሴቶች፣ መምህራንና የመንግስት ሰራተኞች፣ የግሉ ዘርፍ ተቀጣሪና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ ወጣቶች፣ ዕድሮች፣ በባህልና በሙያ የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተፈናቃዮች በሀገራዊ ምክክሩ ተሰታፊ እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል።

እያንዳንዱ የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍልም በዋናው ሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተዋካዮችን በመለየትና አጀንዳዎችን በመስጠት በኩል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ነው የጠየቁት።

የኮሚሽኑ ኮሚሸነር ብሌን ገብረ-መድህን በበኩላቸው፤ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ግልፅ ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።

ይህም ከማንኛውም ውስጣዊና ውጫዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ ስራዎችን ማከናወን የሚያስችል እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አይሮሪት መሐመድ፤ ሂደቱን ለተሳታፊዎች ልየታ መሳካት ተቋማዊ የሰው ሃይልና የቁሳቁስ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሀገር አንድነት የሚበጁ የምክክር አጀንዳ በማቅረብ ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቀጥለው ዓመት ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ማቀዱን መግለፁ ይታወቃል።

ለዚህም በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች የተጠናቀቀ ሲሆን በቀሪዎቹ ክልሎችም በቀጣይ ጊዜያት እንደሚከናወን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም