የማዕድን ዘርፍ በማልማት አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ማዕድን ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ዘርፍ በማልማት አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ማዕድን ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ በተያዘው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ኃብት በማልማት አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ኃብታሙ ተገኝ ገለጹ።
የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸምና ከ2016-2018 ዓ.ም የሚተገበረው የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ኃብታሙ ተገኝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ሰፊ ኃብት ያላት ቢሆንም የሚጠበቅባትን ያክል አልተጠቀመችበትም።
ለማዕድን ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆንና የጸጥታና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በምክንያትነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የማዕድን ኃብቷን ለማልማት የሄደችበት ርቀት በወርቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ አገሪቱ ፔትሮሊየም፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ብረት፣ ፖታሺየምና ሊትየምና ሌሎች ያልተነኩ የከበሩ ማዕድናት እንዳላት አብራርተዋል።
በዘርፉ የአገር ውስጥና የውጭ ትላልቅ ኩባንያዎች በስፋት በማስገባት እነዚህን ኃብቶችን አልምቶ ለመጠቀም ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል።
በባህላዊ በወርቅ ምርት ላይ ላይ ተንጠልጥሎ እንደ አገር ከዘርፉ የታሰበውን ገቢ ለማግኘት እየተሄደበት ያለውን ርቀት ለሕገ-ወጦችና ለምርት ጥራት መጋለጡን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት አራት ፋብሪካዎች የወርቅ ምርትን በብዛትና በጥራት አምርተው ለገበያ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰራ ሲሆን አንድ ፋብሪካ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
ይህም አገሪቱ ከዘርፉ ለማግኘት ያቀደችውን ገቢ ለማሳደግ የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው በተያዘው በጀት ዓመት አገሪቱ የዘርፉ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።