ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከ3 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች የክህሎት ሥልጠና ተሰጥቷል - ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከ3 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች የክህሎት ሥልጠና መሰጠቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የአሥር ዓመት እቅድ የመጀመሪያው መካከለኛ ዘመን ዋና ዋና አፈጻጻምና የቀጣይ መካከለኛ ዘመን ዋና ዋና ግቦች የሚኒስትሮች የውይይት መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን እና ከዛ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

 
ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቁመው ይህም በዘርፉ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ያሳል ብለዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶች መኖራቸውን ገልጸው ይህም በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተለይም በየጊዜው ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ሥልጠና አጠናቀው የሚወጡ ዜጎችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። 

ይህንን ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ ሚኒስቴሩ በትኩረት እንደሚሰራ ነው አጽንዖት የሰጡት። 

ጎን ለጎንም የገበያውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የክህሎት ልማት ሥራ ለማጠናከር የሚያስችል የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ይህንንም ተከትሎ የተሰጡ የተለያዩ አጫጭር የክህሎት ሥልጠናዎች ጥሩ አፈጻጸም አሳይቷል ብለዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ከአንድ ሚሊየን ያነሰ አጫጭር ሥልጠናዎች ይሰጡ እንደነበር አንስተው አሁን ላይ ይህ አሃዝ እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት። 

ለአብነትም በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከ3 ሚሊየን ለሚልቁ ዜጎች አጫጭር የክህሎት ሥልጠናዎች በተለያዩ ዘርፎች መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል። 

በተጓዳኝም የኢንዱስትሪ ሠላም ጋር በተያያዘ በተለይም የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነትን ለማሻሻልና ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት በልሹ አሰራርን ለማስቀረትና የዜጎችን ደኅንነት ለማስከበር  በሚያስችል መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ ለገበያው ያቀረበችው የሰው ኃይል ብቁና ተወዳዳሪ መሆኑን በጥናት ማረጋገጥ መቻሉንም ገልጸዋል። 

በቀጣይም የመዳረሻ አገራትን ማስፋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ በመጠቆም። 
 
 
 
 
 
 
 
 
  
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም