ዛፍ የማይቆረጥበት፣ ቢቆረጥም በምትኩ አምስት ዛፍ የሚተከልባት የሼህ ሀሰን አነኖ መንደር! - ኢዜአ አማርኛ
ዛፍ የማይቆረጥበት፣ ቢቆረጥም በምትኩ አምስት ዛፍ የሚተከልባት የሼህ ሀሰን አነኖ መንደር!
ጭሮ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ )፡- ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማካሄድ ከጀመረች ወዲህ በመጀመሪያው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ተክላለች።
በተያዘው ክረምትም በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለይም በአንድ ጀምበር የችግኝ ተካላ መርሃ ግብር ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል የራሷን ሪከርድ አሻሽላለች።
በዚህ ሂደት የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ልዩ ውጤት ከተመዘገበባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑም ይጠቀሳል።
በአካባቢው ያፈጠጡና ያገጠጡ ተራራዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፣ በእርከን ስራም የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ተራራዎች ውበት ተላብሰዋል።
ዞኑ ከጥንት ጀምሮ የአካባቢ ልምላሜን የሚጠብቅበት የተለየ ባህል እንደነበረው ከሚያመለክቱ አካባቢዎች መካከል የሼህ ሀሰን አነኖ መንደር ህያው ምስክር ናት።
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ አነኖ በተባለችው መንደር ከ100 ዓመታት በፊት ለዛፎችና የተፈጥሮ ሀብቶች ተቆርቋሪነት የሚሰማቸው ሼህ ሁሴን አነኖ የተባሉ ሰው ይኖሩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ይናገራሉ፡፡
የሼህ አነኖ የቀድሞ የኃይማኖት ተማሪ አቶ አብደላ አህመድ፣ ሼህ ሀሰን በመንደሩ የሃይማኖት መምህር የነበሩ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዛፎች ትኩረት እንዲሰጡ ሲያስተምሩ የነበሩና ዛፍ መትከል እንጂ መቁረጥ እንደማይገባ ይቆጣጠሩ ነበር ይላሉ፡፡
ለተማሪዎቻቸውም ''ተገቢውን ትምህርት እንድታገኙ የምታርፉበት ጥላ የሚሆን ዛፍ ያስፈልጋችኋል ብለው ዛፍ በብዛት የመትከል ባህል እንዲያዳብሩ ያስተምሯቸዋል'' ብለዋል።
በዚሁ መነሻነት የጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ ነዋሪዎች መንደሯን አነኖ መንደር ብለው በመሰየም ታሪካቸው እንዳይረሳ አሻራ አኑረዋል፡፡
ሼህ ሀሰን ከችግኝ ተከላው ባሻገር በአካባቢው ውሃ ማቆር የሚችሉ ኩሬዎችን ጭምር ለአካባቢው ማህበረሰብ ያስተዋወቁ እንደነበር አስታውሰዋል።
የሼህ ሀሰን አነኖ መንደር ነዋሪዎች ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዛፍ አይቆርጡም፤ ቤታቸውን የሚቀልሱትም በድንጋይ ካብ ነው ይላሉ አቶ አብደላ።
በዚህም በሼህ ሀሰን አነኖ መንደር አቅራቢያ የሚገነቡ ቤቶችም ይሁን፣ አጥርም ሲገነባ በድንጋይ ካብ እንዲሆን መሰረት ጥለው ያለፉ 'የተፈጥሮ ሀብት መሃንዲስ' ተብለው የሚሞካሹ ግለሰብ እንደነበሩም አንስተዋል።
እስከ ዛሬ ድረስም በአነኖ መንደር ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች፣ መስጂዶች፣ የእህል ጎተራዎች ሳይቀር በድንጋይ ተገንብተው ይገኛሉ፡፡
በዚህ መንደር የቀድሞውን የሼህ ሀሰን አስተምህሮ ሳይለቁ አስከ አሁን ድረስ አንድ ዛፍ የቆረጠ ሰው በምትኩ አምስት የመትከል ግዴታ እንዳለበት የሚያስገድድ ደንብ እንዳላቸው የቀድሞ ተማሪያቸው አቶ አብደላ ያስረዳሉ፡፡
የሼህ ሀሰን አነኖ የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሼህ አሚን ሼህ ሀሰን በበኩላቸው ''አባታችን በግብርና፣ በችግኝ ተከላ፣ በሃይማኖት ትምህርትና ስነ-ጽሁፍ ማህበረሰቡን በማስተማር ታሪክ አስቀምጠው ያለፉ ናቸው'' ይላሉ፡፡
በአባታችን የታነፁት የድንጋይ መስጂዶችና መኖሪያ ቤቶች ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የታሪክና የቅርስ አካል መሆን የሚችሉ ናቸው ይላሉ ሼህ አሚን፡፡
ሼህ አሚን እንደሚሉት የአነኖ መንደር ጉምቢ ቦርደዴ ውስጥ ካሉት አካባቢዎች ሁሉ አረንጓዴና የተስተካከለ ነፋሻማ አየር ያላት ምቹ አካባቢ በማድረግ ለትውልድ አስተላልፈዋል።
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልዪ ከሊል፣ የአነኖን መንደር የተፈጥሮ ጥበቃ ተቆርቋሪነት በሁሉም አካባቢ ማህበረሰቡ ባህል አድርጎ እንዲተገብረው የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በረሃማው ጉምቢ ቦርደዴ ድርቅንና የጎርፍ አደጋን መከላከል የሚችል ምርትና ምርታማነት የሚጨምርበት፤ ዛፍ የሚተከልበት እንጂ የማይቆረጥበት ለማድረግ የሼህ ሀሰን አነኖን ተሞክሮ ለማስፋት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በዞኑ ለግብርና ስራ ምቹ ባልሆነ መልክዓ ምድር ላይ እርከን በመስራት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው በተከታታይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ ናቸው።
በዞኑ በ238 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተሰራ የእርከን ስራም ከደን ዛፍ አንስቶ የተለያየ ጥቅም ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ መሆኑንም ገልጸዋል።