የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልን ጨምሮ የትምህርት ጥራት ችግሮችን መቅረፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው-የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልን ጨምሮ የትምህርት ጥራት ችግሮችን መቅረፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው-የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልን ጨምሮ የትምህርት ጥራት ችግሮችን መቅረፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም እና የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሴክተሩ ዋነኛ ችግር ከጥራት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱን ከስርቆት የፀዳ በማድረግ በኩል የተከናወኑ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ይህም ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት ይዘው ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን እንዲሸጋገሩ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የመምህራን እና ርዕሳነ መምህራን ብቃት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ማሳደግ የሚያስችሉ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ተናግረው ይሕም ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት አለመሟላትም እንደ ሀገር የትምህርት ጥራት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ዋነኛ ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመማሪያ ክፍል፤ ተማሪ ጥምርታ ችግሮች፤ በቂ የሆነ የውሃና የመታጠቢያ ቦታዎችና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም የትምሀርት ጥራት ለማምጣት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በቀጣይ አዲስ በሚሰሩ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ላይ በቂ የሆነ የመሰረተ ልማት እንዲኖር በማድረግ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ያሉትን 50 ሺህ የሚደርሱ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሳደግ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውንም አመልክተዋል።