የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ባደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን ድል ኮርተናል- የመቀሌ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ባደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን ድል ኮርተናል- የመቀሌ ነዋሪዎች
መቀሌ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ባደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን ድል ኮርተናል ሲሉ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን በቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ተደጋጋሚ ድሎችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ይሀንኑ ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በህብረት በመስራት እያስመዘገቡ ያለው ድል የህዝቦች የቆየ አንድነት፣ መተሳሰብና መተባበር መገለጫ ነው።
የከተማው ነዋሪ አቶ መኮንን ተሾመ እንዳሉት አትሌቶቻችን በ19ኛው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደተለመደው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸው አጅግ የሚያኮራ ነው።
አትሌቶቹ በቡድን በመስራት ያስመዘገቡት ድል የሀገር ፍቅር የማስረጽ ስሜቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
"የኮከብ አትሌቶቻችን ድል የኢትዮጵያዊያንን የይቻላል መንፈስን ያደሰ ነው” ያለው ደግሞ ወጣት አማኑኤል ተክሉ ነው።
ድሉ በህብረት ከተሰራ ለውጤት ለመብቃት እንደሚቻል ያሳየና ወጣቶችን ለማፍራት መሰረት የጣለ መሆኑን ገልጸዋል ።
አቶ ዘማርያስ ገብረ መድህን በበኩላቸው “አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትጠራ አድርጓል” ብለዋል።
ሀገርን በዓለም አደባባይ የሚያስጠሩ ወጣት አትሌቶችን የማፍራት ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።