የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምሩ ኢንቨስትመንትንና የገበያ የአገልግሎት ውድድርን ያሳድጋሉ- የምጣኔ ኃብት ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምሩ ኢንቨስትመንትንና የገበያ የአገልግሎት ውድድርን ያሳድጋሉ- የምጣኔ ኃብት ተመራማሪዎች
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምሩ ኢንቨስትመንትንና የገበያ የአገልግሎት ውድድርን እንደሚያሳድጉ የምጣኔ ኃብት ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡
የሀገር ውስጥ ባንኮች በፋይናንስና ቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማጎልበት በገበያው ለመቀጠልና ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓመታት በሀገር ውስጥ የግልና የመንግስት ባንኮች ብቻ ተይዞ የነበረውን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ተቋማት ክፍት በማድረግ ገበያውን ማሳደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በቀጣይ አምስት ዓመታት በትንሹ አምስት ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቃድ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መግለፁ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ተመራማሪ ዶክተር አቡሌ መሀሪ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የሚሰማሩ ባንኮች በካፒታልና በቴክኖሎጂ የተሻለ አቅም ያላቸው መሆኑ የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥን ያሻሽላል፡፡
የውጭ ባንኮች በዘርፉ ልምድና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን የያዙ መሆናቸው ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የልማት ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ደረጀ ደጀኔ ናቸው።
እንደተመራማሪዎቹ ገለጻ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ መሰማራታቸው፤ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ ቀልጣፋና ደንበኛ ተኮር አገልግሎት ለመስጠት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማስፋት ዕድል ይፈጥራል።
በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ከሚባሉ 20 ባንኮች መካከል የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ከመጨረሻዎቹ አምስቱ መሆናቸውን የገለጹት የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች፤ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የውጭ የፋይናንስ ተቋማት የተሳለጠ አገልግሎት የመስጠትና ተደራሽነትን የማረጋገጥ ሰፊ አቅም ያላቸው መሆኑ የሀገር ውስጥ ባንኮችን አቅም ሊፈትን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ተሳትፎ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን አቅም በማጠናከር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሚያሳደግ መልኩ መተግበር እንዳለበት የገለጹት የልማት ኢኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ሞላ አለማየሁ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ወስደው በአፋጣኝ የተሟላ ስራ እንዲጀምሩ ህጎችን ማስተካከልና ቀልጣፋ አሰራሮችን ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 34 በመቶ የባንክ ቅርንጫፎች በአዲስ አበባና በዙሪያው እንደሚገኙ የገለጹት ተመራማሪዎቹ፤ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ካላት አንድ ባንክ ለ25 ሺህ ሰው ምጣኔ አንፃር ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የተገልጋይና የባንክ ቅርንጫፍ ምጥጥንን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸውም ነው ያነሱት ምሁራኑ።
ሆኖም የውጭ ባንኮች የባንክ ገበያውን በመቆጣጠር የሀገር ውስጥ ባንኮችን ከውድድር እንዳያስወጧቸው ትብብርን መሰረት ያደረገ የፋይናንስ አሰራርን ሊተገብሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
አያይዘውም የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ለኢንቨስትመንት ሲመጡ እድልም ስጋትም እንደሚኖረው ነው ተመራማሪዎቹ ያስረዱት።
ለአብነትም በኢንዶኔዥያና ታይላንድ የተሰማሩ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው እንዲገታና ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸው መዘንጋት እንደሌለበት በመጠቆም።
በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ባንኮች ምቹ የሥራ ምህዳር ከመፍጠር ባለፈ ከመስመር እንዳይወጡና ያልተገባ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይፈጥሩ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡