የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመግታት ከሚወሰደው እርምጃ ባሻገር ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከርና የገበያ አማራጮችን ማስፋት ይገባል - የምጣኔ ሃብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመግታት ከሚወሰደው እርምጃ ባሻገር ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከርና የገበያ አማራጮችን ማስፋት ይገባል - የምጣኔ ሃብት ምሁራን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመግታት ከሚወሰደው እርምጃ ባሻገር ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከርና የገበያ አማራጮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ።
የኢኮኖሚ አሻጥር በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ቢሆንም በገበያው ላይ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረግ አንዱ ማሳያ ነው።
የዜጎችን የመግዛት አቅም በማዳከም በግብይቱ ላይ ችግር መፍጠር ወይም ከሚፈለገው በላይ በማቅረብ የመግዛት ፍላጎት እንዳይኖር መስራትም ሌላኛው ምክንያት እንደሚሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
ምርቶችን ያለአግባብ ማከማቸት፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ፣ ጥቁር ገበያ እና ሌሎችም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀሚያ ስልቶች ተብለው ይጠቀሳሉ።
በመሆኑም የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የተረጋጋና ጤነኛ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል የምጣኔ ሃብት አሻጥሮችን በፖሊሲና በአሰራር ጭምር በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረትም የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በአግባቡ አለመተግበር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎችም በዘርፉ ምሁራን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
በዚሁ ጉዳይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ፤ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረት አይነተኛው ምክንያት የኢኮኖሚ አሻጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በአገር ውስጥ በቂ ምርት እያለ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ ነጋዴዎች ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰው የትርፍ ህዳግ በግልጽ አለመታወቅ ነጋዴዎች በፈለጉት የትርፍ መጠን እንዲሸጡ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም አምራቹና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት በአዲስ አበባ የተጀመረውን የእሁድ ገበያ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የገለፁት።
የኢኮኖሚ አሻጥር በተለያየ መንገድ የሚፈጠር ቢሆንም በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የገበያ አለመረጋጋት ነጋዴው አንዱ የችግሩ ምንጭ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ሌላኛው የዘርፉ ምሁር ዶክተር ሞላ አለማየሁ ናቸው።
በመሆኑም ለችግሩም ዋናው የመፍትሄ አካል ነጋዴው መሆኑን ጠቅሰው መንግስትም የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጠረውን አሻጥር በመከላከል ሂደትም የህብረተሰቡ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ዶክተር ሞላ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አረጋ ሹመቴ፤ የሰላምና መረጋጋት እጦትና የግጭት መበራከት ለምጣኔ ሃብት ቀውስ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመግታት መንግስት ሰላምና ጸጥታ ማስከበርና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የአሰራር ብልሹነት ለማስተካከል በጥናት ላይ የተመሰረተ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የዋጋ ግሽበትና የኢኮኖሚ አሻጥር አለምን እየፈተነ ያለ ችግር ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ደግሞ ተጽእኖው ቀላል አለመሆኑን ያስረዳሉ።
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ፤ ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከርና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የገበያ አማራጮችን ማስፋት ይገባል ብለዋል።
የመንግስትን የማስፈጸም አቅምን ማሳደግና የህግ የበላይነትን ማስፈን የችግሩ አይነተኛ መፍትሄ እንደሚሆን ዶክተር አረጋ ሹመቴ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለማርገብ በቅርቡ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።