በአዲስ አበባ ከተማ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ስራ ነገ ይጀመራል-የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ስራ ነገ ይጀመራል-የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) ፦ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ስራ ነገ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የልየታ ስራውን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በተሳታፊ ልየታ ሂደቱ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የወረዳ አስተዳደር እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የተሳታፊ ልየታው በወረዳ የሕብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ በሁለት ምዕራፍ እንደሚከናወን ጠቅሰው ለተባባሪ አካላት ስልጠና መስጠትና የተሳታፊ ልየታን የመምራትና የማስተባበር ሂደቱን ውጤታማነት የመከታተል ስራ ይከናወናል ብለዋል።
በከተማ አስተዳድሩ ስር ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን በማስመረጥ፣ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትና በዋና ምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን እንዲመረጡ እንደሚደረግ ምክትል ኮሚሽነሯ አመልክተዋል።