ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጎልበት ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች - አምባሳደር እፀገነት በዛብህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጎልበት ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች - አምባሳደር እፀገነት በዛብህ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሰራ በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ገለጹ።
አምባሳደር እፀገነት ለዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሹመት ደብዳቤያቸውን ኢንቴቤ በሚገኘው ቤተ-መንግስት አቅርበዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሯ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተላከ የሰላምታና የመልካም ምኞት መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ ማቅረባቸውን ኢዜአ ካምፓላ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር እፀገነት ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂካዊ መሆኑን ገልጸው በሁለቱ አገራት መካከል የባህልና የተፈጥሮ ተመሳሳይነት መኖሩን አንስተዋል።
በዩጋንዳ ቆይታቸው አገራቱ ያላቸውን የዳበረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ የሕዝብ ለሕዝብ እንዲሁም የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ ለዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ገልጸውላቸዋል።
የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አገራቱ በሁለትዮሽ፣በክልላዊ እና ዓለም ዓቀፍ ጉዳዩች ላይ በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸው ያላቸውን የባህልና የቋንቋ ትስስርም አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቱም አምባሳደሯ በዩጋንዳ የተሳካ የስራ ቆይታ እንዲኖራቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።