በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2015 (ኢዜአ) :- በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የማጣሪያ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ያለው ሻምፒዮና ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።
ከረፋዱ 5 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በሚካሄደው የ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ አትሌት ሀብታም ዓለሙ፣አትሌት ወርቅነሽ መለሰ እና አትሌት ትዕግስት ግርማ ይወዳደራሉ።
በሰባት ምድቦች በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከእያንዳንዱ ምድብ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አትሌቶች ከነገ በስቲያ ለሚካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ2 ደቂቃ የ5000 ሜትር ሴቶች የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል።
በምድብ አንድ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ እና አትሌት መዲና ኢሳ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።
በምድብ ሁለት በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ይሳተፋሉ።
ከሁለቱ ምድቦች ከ1 እስከ 8 የሚወጡ አትሌቶች ቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ያልፋሉ።
የ5000 ሜትር ሴቶች የማጣሪያ ውድድር ከቀኑ 6 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ መደረግ የነበረበት ቢሆንም በሀንጋሪ ባለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ምክንያት የሰዓት ሽግሽግ እንደተደረገበት የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ53 ደቂቃ በ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል።
በምድብ አንድ አትሌት ሎሚ ሙለታ፣በምድብ ሁለት አትሌት ሲምቦ አለማየሁ እና በምድብ ሶስት አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ ይወዳደራሉ።
ከእያንዳንዱ ምድብ ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች እሁድ ነሐሴ 21/2015 ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሻምፒዮናው 1 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 6 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።