ቀጥታ፡

የአትሌቶቻችን ድል ኅብረትና አንድነት ለውጤት እንደሚያበቃ አስተምሮናል---በአፋር ክልል የስፖርት ዘርፍ አካላት

ሰመራ ነሐሴ 16/2015(ኢዜአ):- አትሌቶቻችን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እያስመዘገቡት ያለው ድል ኅብረትና አንድነት ለውጤት እንደሚያበቃ አስተምሮናል ሲሉ በአፋር ክልል የስፖርት ዘርፍ አካላት ተናገሩ።

የስፖርት ቤተሰቦቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ በዓለም አደባባይ ውጤታማ ያደረጋቸውን ትብብርና ቅንጅት የሀገር ዕድገትን ለማፋጠን ማዋል ይገባል።

የአትሌቶቻችን ድል አገራችን በዓለም አደባባይ ያደመቀ፣ ሰንደቋን ከፍ ያደረገና አንድ ስንሆን ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየ ነው ሲሉም የስፖርት ቤተሰቦች ተናግረዋል።

የአፋር ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡመር መሐመድ አትሌቲክሱ ለአገር ገፅታ ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ሲታይ የሚፈጥረው ስሜት ከምንም  በላይ እንደሆነም ነው የገለፁት።

የሀገር ምልክት የሆኑት አትሌቶች ለሀገራቸው በአንድነት ከሚቆሙባቸው የስፖርት ዓይነቶች አትሌቲክስ አንዱ መሆኑንም አቶ ኡመር ተናግረዋል።


 

የአትሌቶቹ ውጤት አንድነትን የሚያጠናክር ነው ያሉት ደግሞ ደግሞ የአሚበራ ወረዳ የወጣቶች እና ስፖርት ባለሙያ የሆነው ወጣት መሐመድ አብዱ ነው።  

ድሉ የህብረት ውጤት እንደሆነ አቶ መሐመድ ገልጸው፣ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትብብር የተገኘን ውጤት በቀጣይም አንድነትን በማጠንከር በሌሎች የልማት ሥራዎች ለመድገም ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ የወጣቶችና ስፖርት ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ አህመድ ኑር በበኩላቸው በተመዘገበው አመርቂ ውጤት መደሰታቸውን ገልፀዋል። 

"የአገራችን ሰንደቅ በዓለም ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚፈጥረው ልዩ ስሜት የአገራችንን ህዝቦች አንድ እንደሚያደርግ በተገኘው ድል በሚገባ ተረድቻለሁ" ብለዋል።


 

"አትሌቶቹ ያስመዘገቡት ድል ህብረት ካለን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው" ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባለሙያ አቶ ያሲን አህመድ ናቸው።

ከተባበርን ሌሎች ሀገራዊ ድሎችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ከአትሌቶቹ ውጤት በመማር ኢትዮጵያን በአንድነት ሰርተን በሌላውም ዘርፍ ለውጤት መትጋት አለብን ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በቡዳፔስት፤ ሐንጋሪ በመካሄድ ላይ ባለው 19 ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ላይ ስትሆን፣ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የሴቶች የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት አስደማሚ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል።


 

እስከ ቀጣዩ እሁድ በሚቀጥሉት ውድድሮችም አትሌቶቿ በቡድን ሥራ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም