ቀጥታ፡

በአገሪቱ በመንግሥትና በግል ባለሃብቶች የተሰሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር አድርገዋል - የቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2015 (ኢዜአ) :- በአገሪቱ በመንግሥትና በግል ባለሃብቶች የተሰሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር ማስቻሉን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።    

የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸምና ከ2016-2018 ዓ.ም የሚተገበረው የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደተናገሩት የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የጸጥታ ጉዳዮች በዘርፉ የተያዘው እቅድ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።  

ይሁንና በ2015 በዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን የቱሪስት ፍሰቱም ከቅድመ ኮቪድ ወደ ነበረበት መመለስ መቻሉን ገልጸዋል።

ዘርፉን ለማነቃቃት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በዚህም በመንግሥትና በባለሃብቶች የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።


  

''በመጪዎቹ ዓመታት ከአስር በላይ የቱሪስት መዳረሻዎች ይገነባሉ ተብሎ ይታሰባል'' ያሉት ሚኒስትሯ የነበሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ ትኩረት ይደረግበታል ብለዋል። 

በተጨማሪም  በዘርፉ የግል ባለሃብት ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግም ይሰራል ነው ያሉት። 

እየተገነቡ ባሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዙም ተናግረዋል። 


 

በቀጣይ ዓመታት ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና የመሆኗን ዕድል በመጠቀም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስፋትና በዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

በተጓዳኝም እያደገ የመጣውን የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር የማሳደግ ሥራም በቀጣዮቹ ዓመታት ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች መሆናቸውን  ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም