ቀጥታ፡

ቻይና ከአፍሪካ አገራት ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች - በአፍሪካ ኅብረት የቻይና አምባሳደር ሁ ቻንግቹን 

አዲስ  አበባ ፤ነሐሴ 16/2015(ኢዜአ):-ቻይና ከአፍሪካ አገራት ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቻይና አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ገለጹ።

በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቻይና አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ቻይና በአፍሪካ ኅብረት ሥር እየተወጣች ስላለው ተልዕኮ በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ሁ ቻንግቹን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ምጣኔ ኃብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። 

አሁን ላይም ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር በድኅነት ቅነሳ፣ በትምህርት፣ በሥልጠና፣ በጤና፣ በልማትና በሌሎችም የትብብር መስኮች በጋራ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቻይና የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና ተግባራዊነትን በማገዝ አህጉሪቷ በንግድና ኢንቨስትመንት ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት እየደገፈች ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ቻይና ከምትከተለው የእድገት እቅድ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን አንስተው ፤ አገሪቷ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል። 

ቻይና በሮድ ኤንድ ቤልት የልማት ኢኒሼቲቭ በአፍሪካ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን አፍሪካ ያለባትን የመሰረተ-ልማት ክፍተት ለመሙላት እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።  

በመሆኑም በቀጣይም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የጋራ የትብብር መስኮች የጋራ ተጠቀሚነት ባረጋገጠ መልኩ አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም