ቀጥታ፡

የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በ2015 በጀት ዓመት 1 ሺ 472 ደረጃዎችን አጽድቋል - የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት

አዲስ  አበባ ፤ነሐሴ 16/2015(ኢዜአ)--በ2015 በጀት ዓመት የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ዘርፎች 1 ሺህ 472 ደረጃዎች ማጽደቁን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት የተወጣጡ 205 ብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ደረጃዎችን የሚያዘጋጅ ብሔራዊ የደረጃዎች ድርጅት ነው። 

ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክ ኮሚቴዎቹ በጋራ የተስማሙባቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎችን የመጨረሻ ረቂቅ ሰነዶች ዝርዝር እንዲያፀድቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ለተሰጠው 15 አባላት ላሉት የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸድቃል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2015 በጀት ዓመት በተካሄዱ ሦስት የብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ጉባኤ 1 ሺህ 472 ደረጃዎች ጸድቀዋል።

ደረጃዎቹ የጸደቁት ጤናና አካባቢ ደኅንነት፣ ኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ ምግብና የግብርና ውጤቶች፣  መሰረታዊና አጠቃላይ ዘርፍ፣  በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና፣  ጨርቃጨርቅና ቆዳ ዘርፍ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም መሰረት 451 አዲስ ደረጃዎችና በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ በቴክኖሎጂ ለውጥ ምክንያት የተከለሱ 387 ደረጃዎች መሆናቸውና መጽደቃቸውን ገልጸዋል።

634 የተለያዩ ደረጃዎች ደግሞ የዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማየት ለቴክኒክ ኮሚቴዎች ቀርበው ግምገማ ተደርጎባቸው ባሉበት እንዲቀጥሉ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ማጽደቁን ተናግረዋል። 

ከጸደቁት የኢትዮጵያ ደረጃዎች በጤናው፣ በምግብና እርሻ፣ በኮንስትራክሽን፣ የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች በአጠቃላይ 55 አስገዳጅ ደረጃዎች ሆነው መጽደቃቸውንም አመላክተዋል።

የጸደቁት አስገዳጅ ደረጃዎች የኅብረተሰብ ጤና እንዲጠበቅና ንግድን ለማሳለጥ እንደሚያስችሉ ጠቁመዋል።  

ኅብረተሰቡ ለጥራት ትኩረት እንዲሰጥና አምራቾችም የወጡ ደረጃዎችን በኃላፊነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በ50 ዓመታት ውስጥ 11 ሺህ 890 ያክል አጠቃላይ ደረጃዎችን ያወጣ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 350 ደረጃዎችን በአስገዳጅነት አጽድቋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም