ቀጥታ፡

የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2015 (ኢዜአ):-የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሰረት ገለጹ።

ሌተናል ጀኔራል መሰለ ከምስራቅ ወለጋ የዞንና የሁሉም ወረዳ አመራሮችና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎች ውይይት አድርገዋል።

“የሸኔ ቡድን በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ እየዘረፈና ንፁሃንን እየገደለ የማህበረሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲያውክ ነበር” ብለዋል ሌተናል ጀኔራሉ።


 

አሁን ላይ ቡድኑ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በሰራዊቱ፣ በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሺያ የተቀናጀ እርምጃ ከባድ ኪሳራ እየደረሰበት ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

“የጠላትን አጠቃላይ ሁኔታና ፍላጎት በማጥናት አደረጃጀቱን በማፍረስ እንቅስቃሴውን በመቆጣጠር የሰላም ስጋት መሆኑ እስኪያበቃ በጋራ ይሰራል” ነው ያሉት የዕዙ አዛዥ።

የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ እየተሰራ ባለው ያልተቋረጠ ኦፕሬሽንና እየተገኙ ላሉ ድሎች የአካባቢው ማህበረሰብ ከሰራዊቱ ጎን ሆኖ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

በቀጣይም ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ በአጭር ጊዜ አካባቢውን ከቡድኑ ነጻ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ሌተናል ጄነራሉ አሳስበዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋጋሪ ነገራ በበኩላቸው “ቡድኑ ግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ሳይኖረው መንገድ በመዝጋት የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማወክና ከልማት አስተሳሰብ በማስወጣት ዘረፋና ግድያ የሚፈፅም ኃይል በመሆኑ ቡድኑን ማጥፋት አማራጭ የሌለው ቀዳሚ ተግባር ነው” ብለዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለሜሳ ኦልጅራ በበኩላቸው ቡድኑ አሁን ላይ በመከላከያ ሰራዊቱ፣ በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሺያ የተቀናጀ እርምጃ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

የደረሰብትን ኪሳራ ለመሸፈን “ቅርፁን ቀይሮ በከተሞችና በመንግስት መዋቅሮች ሴሎችን አስርጎ በማስገባትና ሕዝብ እንዳይረጋጋ ራሱን በማጋነን ውዥምብር ከመፍጠርና ከተራ ዘራፊነት ያለፈ አቅም የሌለው ነው” ብለዋል።


 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮች በበኩላቸው ታጥቆ የአካባቢውን ሰላም የሚያውከውን ሸኔን ለማጥፋት እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ሰራዊቱ ግዳጁን ሌት ተቀን ያለ እረፍት በአስቸጋሪ መልክዓ-ምድርና የአየር ፀባይ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በውይይቱ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም