ቀጥታ፡

የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው - የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር

አምቦ፤ ነሐሴ 16/2015(ኢዜአ)፡- ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡


በዞኑ አደኣ በርጋ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 18 የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ፡፡ 


በተጠናቀቁት ፕሮጀክቶችም ከ100ሺህ በላይ የሚሆኑ የወረዳው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

 
ፕሮጀክቶቹን  የዞኑና የወረዳው የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት መርቀው የከፈቱት የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እና የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አድማሱ ጣሰው ናቸው።


ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ህንጻ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤቶች እና የመንገድ ግንባታዎች ይገኙባቸዋል፡፡

 




ዋና አስተዳዳሪው አቶ ዲዳ ጉደታ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች  እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው፡፡


ፕሮጀክቶቹ  የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል የጎላ ፋይዳ ስላላቸው ተጠቃሚው ህብረተሰብ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል፡፡


ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለውሸት ፕሮፓጋንዳ እጅ ሳይሰጥ ልማቱን እንዲያፋጥንም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡


የአደኣ በርጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አድማሱ ጣሰው በበኩላቸው በወረዳው ተመርቀው ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት እነዚሁ የልማት ፕሮጀክቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የወጣባቸውና ይህም በክልሉ መንግስት በጀትና በወረዳው ህዝብ ተሳትፎ የተሸፈነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡


 


ፕሮጀክቶቹ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩም ተናግረዋል፡፡


የወረዳው ነዋሪ አቶ ቢቂላ መገርሳ በሰጡት አስተያየት ግንባታዎቹ የመልካም አስተዳደር ችግርን የፈቱ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው ፕሮጀክቶቹ ረዥም ግዜ እንዲያገለግሉ እንክብካቤ እናደርጋለን ብለዋል፡፡  


በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የዞንና የወረዳው አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም