ቀጥታ፡

የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርትና ምርታማነት በመጨመር፣ የሥራ እድል በመፍጠርና የወጭ ንግድ በማሳደግ ከፍተኛ እምርታ አስመዝግቧል -  ዶክተር ግርማ አመንቴ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2015 (ኢዜአ) ፦ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርትና ምርታማነት በመጨመር፣ የሥራ እድል በመፍጠርና የወጭ ንግድ በማሳደግ ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገቡን የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ። 

የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም እና ከ2016-2018 የሚተገበረው የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ሲቀመጥ የግብርናው ዘርፍ እድገት በአገር አቀፍ ደረጃ በአማካይ 6 በመቶ እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱ ጠቁመዋል። 

ይህንንም ተከትሎ የግብርና ዘርፍ ላለፉት ሦስት ዓመታት የ5 ነጥብ 5 በመቶ፣ የ6 ነጥብ 1 በመቶ እና የ6 ነጥብ 3 በመቶ ዓመታዊ እድገት በተከታታይ ማስመዝገቡን ተናግረዋል።   

በዚህም የግብርናው ዘርፍ በመሪ እቅዱ የተቀመጠለትን አማካይ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።


 

ዕድገቱን በቀጣይ ዓመታትም ማስቀጠል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።   

በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገበው ስኬት በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተወሰዱ አዳዲስ አርምጃዎች (intiatives) ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል።


 

ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያደርገው የአዝዕርትና የሆርቲካልቸር መስክ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የኩታ ገጠም እርሻን ማስፋት መቻሉ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ማረስ መቻሉን ጠቁመው ይህም አርሶ አደሩ ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ፣ ግብዓትና የሙያ ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሏል ነው ያሉት።

የግብርና ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡና ባንኮችም የብደር አቅርቦታቸውን እንዲያሰፉ መደረጉ አርሶ አደሩ በትራክተርና በኮምባይነር የግብርና ሥራውን እንዲከውን ማስቻሉን ገልጸዋል።     

ለአብነትም በ2015 ወደ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር መታረሱን ጠቁመዋል። 

ይህንን ተከትሎ አሁን ላይ የቢራ ገብስና ስንዴ ከውጭ ማስገባት ቆሟል ያሉት ሚኒስትሩ ከውጭ የሚገባውን ሩዝ ከግማሽ በላይ በአገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉንም ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች እንዲጨምሩ መደረጉን ጠቁመው የአቮካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል። 

የሌማት ትሩፋትም በተለይ የሥጋ፣ የወተት፣ የማር እና የአሳ ምርት ከዚህ ቀደም ከነበረው የምርት ምጣኔ አኳያ ሲታይ ትልቅ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በድምሩ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የሥራ እድል በመፍጠርና የወጭ ንግድ በማሳደግ ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገቡን አብራርተዋል።    

በዘርፉ የተገኙትን ውጤቶች በማጠናከር ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።  

በተለይም የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሻሻልና አሲዳማ መሬቶችን በማከም ምርትና መርታማነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።   

በተያዘው የ2016 የምርት ዘመን 17 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአገር አቀፍ ደረጃ ለማረስ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ዶክተር ግርማ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም