የ19ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዎና ደጋሹ የቡዳፔስት ስታዲየም

 

የቡዳፔስቱ ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ተገንብቶ ዝግጅቱን አሟልቶ እንዲያስተናግድ በሚያስችል ቁመና ላይ የደረሰው ከ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዎና መጀመር ቀደም ብሎ ነው።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚጠቀስ ግዙፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነት ነው።

“የስፖርቶች ንጉስ” የሆነ ውድድር ነው የሚሉትም አልጠፉም።

አገራት ለሻምፒዮናው ከሚያደርጉት ሽር ጉድ ባለፈ እንደዚህ ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የሚያደርጉት ፉክክር ቀላል የሚባል አይደለም።

ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን ለማዘጋጀት ሚሊዮኖችን አለፍ ካለም ቢሊዮኖችን ወጪ ያደርጋሉ።

አገራት ውድድሩን ከማስተናገድ ባለፈ ታሪካቸውንና ባህላቸውን ጨምሮ ያላቸውን መልካም ገጽታ ለመገንባት ይጠቀሙበታል ።

19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከቀናት በፊት በማዕከላዊ አውሮፓዊቷ አገር ሃንጋሪ ተጀምሯል።

በሻምፒዮናው ላይ ከ200 አገራት በላይ የተወጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች እየሳተፋ ይገኛሉ።

ሻምፒዮናው ቡዳፔስት በሚገኘው ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ነሐሴ 13/2015 የሻምፒዮናው ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በዚሁ ስታዲየም ተከናውኗል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣የሀንጋሪ ፕሬዝዳንት ካታሊን ኖቫክ፣ የተርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን፣ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮ፣የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት አሌክሳንዳር ሴፈሪንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ይትወሳል።

እኛም ሻምፒዮናው እየተካሄደበት ስላለው ስታዲየም መረጃዎችን ልናካፍላችሁ ወደናል።

ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም የግንባታ መሰረት ድንጋይ እ.አ.አ በ2020 ተጥሎ ግንባታው የተጀመረው እ.አ.አ 2021 መግቢያ ላይ ነበር።

  • ስታዲየሙ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት 40 ሺህ ተመልካች እንደሚያስተናግድ ይፋ ተደርጎም ነበር።
  • ይሁንና የግንባታው ስራ ሲጀመር በሚይዘው የተመልካች ብዛት ላይ ክለሳ ተደርጎ ስታዲየሙ 36 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግድ መልኩ ግንባታው እንደሚቀጥል ተገለጸ።
  • በዚሁ መሰረት የላይኛው የስታዲየም ክፍል 22 ሺህ እንዲሁም የታችኛው ክፍል 14 ሺህ ተመልካች እንዲደሚይዝ የሃንጋሪ መንግስት አስታወቀ።
  • የስታዲየሙ ግንባታ ከእ.አ.አ 2022 አጋማሽ ዓመት በኋላ ተጠናቆ በዛው ዓመት ማብቂያ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የትኬት ሽያጭ መከናወን ጀመረ።
  • ስታዲየሙ እ.አ.አ ሰኔ 16/2023 የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቆ በይፋ ስራ ጀመረ።
  • አጠቃላይ ለስታዲየሙ ግንባታ 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ወጪ መደረጉንና ይህም ሀንጋሪ ለስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ያወጣችው ትልቁ ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቧል።
  • ከዚህ ቀደም ሀንጋሪ ለስፖርት መሰረተ ልማት ያወጣችው ትልቁ ወጪ ከ67 ሺህ በላይ ተመልካች ለሚያስተናግደው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ሲሆን ለስታዲየሙ ግንባታ 600 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደተደረገበት መረጃዎች ያመለክታሉ።
  • የውድድሩ መሮጫ መም “The Crown of the Queen of Sports” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ስያሜው የመነጨው አትሌቲክስ የሁሉ ስፖርቶች ቁንጮ ነው ከሚል እሳቤ መሆኑን ተገልጿል።
  • ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየምን የገነቡት ‘ዛኤቭ ኢፕቶይፓሪ ዜድአርቲ’  (ZÁÉV Építőipari Zrt)   ‘ማግያር ኢፒቶ ዜድአርቲ’ (Magyar Építő Zrt)  የተሰኙ ተቋራጮች ናቸው።
  • ስታዲየሙ የሚገኘው በደቡብ ማዕካላዊ ቡዳፔስት እና በአውሮፓ በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የዳኑብ ወንዝ ምስራቃዊ አቅጣጫ ነው።
  • ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በኋላ የስታዲየሙ የመያዝ አቅም ወደ 14 ሺህ ዝቅ እንደሚልና በተመልካቾች በኩል ያሉ ጊዜያዊ የስታዲየሙ የላይኛው ክፍል መሰረተ ልማቶች እንደሚነቀሉም ተገልጿል።

የዓለም የአትሌቲክስ አፍቃሪያን በስታዲየሙ በቀጣይ ቀናት በሚካሄዱ የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን በጉጉት መከታተላቸውን ይቀጥላሉ።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው እስከ ነሐሴ 21/2015 ይቆያል።

በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ በሚገኘው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአራተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ከምሽቱ 4 ሰአት ከ30 የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና አትሌት ድርቤ ወልተጂ ይሳተፋሉ።

አትሌት ብርቄ 3 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ94 ማይክሮ ሴኮንድ እና አትሌት 3 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ ያላቸው የግል ምርጥ ሰዓት ነው።

በ3 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው የ29 ዓመቷ ኬንያዊ አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።

አትሌቷ የ1 ማይል እና የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትም ናት።

በዚህ ውድድር ላይ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን ትወዳደራለች።

ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ42 ደቂቃ በ3 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማና አትሌት ጌትነት ዋለ ይወዳደራሉ።

አትሌት ለሜቻ በሰኔ ወር 2015 በፓሪስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በኳታሩ አትሌት ሳይፍ ሰኢድ ሻሂን ለ19ኝ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ1 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮ ሴኮንድ ማሻሻሉ ይታወቃል።

አትሌት ጌትነት 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ ይግል ምርጥ ሰአቱ ነው።

በውድድሩ አትሌት ለሜቻ እና የሞሮኮው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ የሚያደርጉት ፉክክር በስፖርት ቤተሰቡ ከወዲሁ በጉጉት ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እስከ አሁን 1 የወርቅ፣1 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም