የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ የፍትሕ ፍኖተ ካርታ እና አዲሱ የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ በሚቀጥለው ዓመት ስራ ላይ ይውላሉ - ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ - ኢዜአ አማርኛ
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ የፍትሕ ፍኖተ ካርታ እና አዲሱ የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ በሚቀጥለው ዓመት ስራ ላይ ይውላሉ - ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ
አዲስ አበባ ፣ነሃሴ 16/2015 (ኢዜአ):- የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ የፍትሕ ፍኖተ ካርታ እና አዲሱ የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ በሚቀጥለው ዓመት ስራ ላይ እንደሚውሉ የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ገለጹ።
የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም እና ከ2016-2018 የሚተገበረው የሁለተኛው ምዕራፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
በግምገማው ከታዩ ጉዳዮች መካከል የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ሂደትና አፈጻጸም አንዱ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት በመጀመሪያው ምዕራፍ የእቅድ ትግበራ በፍትሕ ዘርፉ ነባር ህጎችን የመቀየር፣ ማሻሻያዎችን የማድረግና አዳዲስ ህግጋትን የማፅደቅ ስራዎች አሳታፊ በሆነ መልኩ ተከናውነዋል።
ሆኖም ከግጭትና አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የህግና የመብት ጥሰቶች መስተዋላቸው፣ የክልሎች የጎንዮሽ ቅንጅት ጠንካራ አለመሆንና የህጎች አፈጻጸም ክፍተቶች በዕቅድ ዘመኑ መስተዋላቸው በድክመት መነሳቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የዕቅድ ዘመን የሽግግር ፍትሕን ጨምሮ አዳዲስ የፖሊሲ አሰራሮችን ለመተግበር እንቅስቃሴ መጀመሩን አንስተዋል።
ለአብነትም ለሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ግብዓት ለመሰብሰብ በሁሉም ክልሎች ከ50 በላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ ፖሊሲው በሚቀጥለው ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
ከዚህም ባሻገር አጠቃላይ የፍትሕ ዘርፍን በመሰረታዊነት የሚለውጥ የሦስት ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
ፍኖተ ካርታው የወንጀል ህግን፣ የአስተዳደር ፍትሕን፣ የፍትህ ዘርፍ የባለሙያዎች ብቃትን ስነምግባርን የማጥራት ስራና ዲጂታይዜሽንን ጨምሮ በርካታ ግቦችን መያዙን ነው ያብራሩት።
ከዚህም ባለፈ የፍትሕ ስራዎች የማህበረሰቡን ባህልና እሴት ባገናዘበ መልኩ እንዲከናወኑ፤ ማህበረሰብ ተኮር የፍትሕ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ የማድረግ ግብ በፍኖተ ካርታው መካተቱን ገልጸዋል።
ዶክተር ጌዲዮን አክለውም የፍትሕ ዘርፉን ይበልጥ ቀልጣፋ የሚያደርግ አዲስ የወንጀል ስነስርዓትና የማስረጃ ህግ በሚቀጥለው ዓመት ፀድቆ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
አዲሱ ህግ ከዚህ በፊት የነበረውን አሰራር የሚያዘመን፣ አማራጭ አካሄዶችን የያዘ፣ ቀልጣፋ እና አዳዲስ አሰራሮችን የሚያስተዋውቅ መሆኑንም ተናግረዋል።