ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2015 (ኢዜአ):- በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ በሚገኘው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአራተኛ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና አትሌት ድርቤ ወልተጂ ይሳተፋሉ።

አትሌት ብርቄ 3 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ94 ማይክሮ ሴኮንድ እና አትሌት 3 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ ያላቸው የግል ምርጥ ሰዓት ነው።

በ3 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው የ29 ዓመቷ ኬንያዊ አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።

አትሌቷ የ1 ማይል እና የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትም ናት።

በዚህ ውድድር ላይ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን ትወዳደራለች።

ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ42 ደቂቃ በ3 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማና አትሌት ጌትነት ዋለ ይወዳደራሉ።

አትሌት ለሜቻ በሰኔ ወር 2015 በፓሪስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በኳታሩ አትሌት ሳይፍ ሰኢድ ሻሂን ለ19 ዓመታት ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ1 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮ ሴኮንድ ማሻሻሉ ይታወቃል።

አትሌት ጌትነት 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።

በውድድሩ አትሌት ለሜቻ እና የሞሮኮው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ የሚያደርጉት ፉክክር በስፖርት ቤተሰቡ ከወዲሁ በጉጉት ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እስካሁን 1 የወርቅ፣1 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም